
ባሕር ዳር: ግንቦት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ከጤና ሚኒስቴር እና ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ዓለም አቀፍ ከወሊድ በኋላ የሚፈጠር ፊስቱላን የማጥፋት ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ ነው፡፡
“ጤናዋ መብቷ ነው፤ ፊስቱላን እና በወሊድ ምክንያት የሚደርሱ ጉዳቶችን ለማስቆም በጋራ እንረባረብ” በሚል መሪ መልዕክት ነው በዓለም ለ14ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ13ኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘው።
በጤና ሚኒስትር የሚኒስትር ድኤታ ከፍተኛ አማካሪ ዮናስ ዙላ ባለፉት 10 ዓመታት በኢትዮጵያ የእናቶች ሞት ምጣኔ በእጅጉ የቀነሰ ቢኾንም አሁንም የእናቶች ሞት ከፍተኛ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡ ብዙ እናቶች (ሴቶች) ከእርግዝና እና ወሊድ ጋር በተያያዙ ችግሮች ምክንያት በአጭር እና በረጅም ጊዜ ሕመም እንደሚሰቃዩም ገልጸዋል።
ከሕመሞች መካከል ከወሊድ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ፊስቱላ አንዱ እንደኾነ ነው የጠቀሱት፡፡
የፊስቱላ ሕሙማን ቁጥር በክልሎች ጉልህ የኾነ ልዩነት አለ ያሉት አማካሪው አጠቃላይ ቁጥሩ ግን እንደቀነሰ ጠቅሰዋል። ለዚህ መቀነስ ምክንያት የተሠሩ ሥራዎች እንደኾኑ ጠቅሰው በርካታ ተግባራት እንደተከናወኑ ነው ያነሱት።
በኢትዮጵያ 19ሺህ በላይ የፊስቱላ ሕሙማን እንዳሉ ያመላከቱት አማካሪው ፌስቱላ ከፍተኛ ትኩረት የሚያስፈልገው የጤና ችግር መኾኑን አስገንዝበዋል።
በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የእናቶች ሕጻናት እና አፍላ ወጣቶች ሥርዓተ ምግብ ዳይሬክተር መልሰው ጫንያለው ክልሉ የፌስቱላ ሕሙማንን በማከም፣ በማሳከም እና በሪፈር ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በመላክ እንደሚታወቅ ተናግረዋል። ችግሮች ቀድመው የተለዩ እና የታወቁ በመኾናቸው ቀድሞ ለመከላከል የተለያዩ ሥራዎች ሲሠሩ እንደቆዩም ጠቅሰዋል።
በማሳየነትም የቤተሠብ ዕቅድ አገልግሎት ሥራን አንስተዋል። መረጃው እስከተሰጠበት ጊዜ ድረስ ባለፉት አራት ዓመታት በክልሉ ከ600 በላይ የፊስቱላ ሕመም የገጠማቸው እናቶች ሕክምና ማግኘታቸውን አንስተዋል።
ከ3ሺህ በላይ የሚኾኑ እናቶች ደግሞ የማሕጸን መውጣት ችግር ገጥሟቸው ሕክምና አግኝተዋል ብለዋል። ከ423በላይ እናቶች ከሕክምና ባሻገር የሥራ መጀመሪያ ገንዘብ ተሰጥቷቸው ወደ ማኅበረሰቡ ተቀላቅለው ሕይወታቸውን የቀጠሉበት ኹኔታ መኖሩንም ጠቅሰዋል።
በዝግጅቱ ፌስቱላን ለመከላከል የተሠሩ ሥራዎች እና እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች ቀርበው ውይይት እየተካሄደባቸው ነው።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
#አሚኮ_ዜና #የፊስቱላ_ሕክምና #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
