
ጎንደር: ግንቦት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር በመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት ተደራጅተው ቦታ ለተወሰነላቸው 550 ማኅበራት “ሳይት እና ብሎክ ቁጥር” ርክክብ እያካሄደ ነው።
በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተደራጅተው የመኖሪያ መገንቢያ ቦታ ሲጠባበቁ ለነበሩ 550 ማኅበራት የክልሉ እና የከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት ነው የሳይት እና ብሎክ ቁጥር የማሳወቅ እና የርክክብ ሥነ ሥርዓት ያካሄደው።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር መሬት መምሪያ ኀላፊ ትዕዛዙ በፅሃ እንደተናገሩት የከተማዋን የቤት ችግር ለመፍታት 456 ሄክታር ቦታ ተዘጋጅቶ ለ550 ማኅበራት ተጠቃሚ እንዲኾኑ ተደርገዋል ብለዋል።
በዚህም ከ13ሺህ 200 በላይ አባዎራዎች ተጠቃሚ እንደሚኾኑም ገልጸዋል።
ማኅበራቱ በተደራጁበት ዓመት መሠረት ነው የቦታ ልየታ እና ርክክብ የተደረገው።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ኅብረት ሥራ ማኀበራት ማስፋፊያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሲሳይ አዳነ በማኅበራቱ ወጣቶችን፣ ሴቶችን፣ አረጋውያንን እና የጸጥታ አካላትን በማካተት ተጠቃሚ ለማድረግ ተሠርቷል ብለዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ለማኅበራቱ ቦታ መስጠት ብቻ ሳይኾን ቤት ሠርተው እንዲኖሩም ከተማ አሥተዳደሩ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
ዛሬ ከተሰጡት ከ550 ማኅበራት በተጨማሪም ለቀሪ ማኅበራት ቦታ እንደሚሰጥ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ቃል ገብተዋል።
የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌትነት አማረ የክልሉን ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት እየሠሩ መኾኑን ገልጸዋል።
ቦታ የተሰጣቸው ማኅበራት የከተማዋን ደረጃ የጠበቀ ቤት በመገንባት ከተማቸውን እንዲያለሙ ኮሚሽነሩ አሳስበዋል።
በመርሐ ግብሩ የተገኙት የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ ሞላ መልካሙ (ዶ.ር) ጎንደር ከተማን የሚመጥን የቤት ግንባታ ያስፈልጋል ብለዋል።
የክልሉ መንግሥት የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት እየሠራ መኾኑን ቢሮ ኀላፊው ጠቅሰዋል።
የክልሉ መንግሥትም ማኅበራዊ ፍትሕን ለማረጋገጥ፣ መሠረተ ልማቶችን ለማሟላት እና ብድር ለማመቻቸት እንደሚሠሩ ቢሮ ኀላፊው ጠቅሰዋል።
ዘጋቢ፦ አገኘሁ አበባው
#አሚኮ_ዜና #የቤት_ማኅበር #ጎንደር #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
