👨‍👩‍👧‍👦 የቤተሰብ እሴቶች መሸርሸር ለማኅበራዊ ቀውሶች አንዱ ምክንያት ነው። 🇪🇹

6

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ “በመልካም ቤተሰብ መልካም ትውልድ፤ ለጸና ሀገር” በሚል መሪ መልዕክት ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ቀንን በክልል ደረጃ ለ4ኛ ጊዜ እያከበረ ነው።

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዝና ጌታቸው እንደገለጹት ቤተሰብ የሀገር መሠረት ነው። ቤተሰብ የሁሉም መሠረት በመኾኑ ሀገርን መለወጥ የሚቻለው ቤተሰብ ላይ ጠንካራ ሥራ ሲሠራ ነው ብለዋል።

ሕጻናት በሥነምግባር ታንጸው መልካም ቤተሰብ እንዲገነባ ከወላጆች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከሃይማኖት ተቋማት የሚጠበቅ ኀላፊነት ነው ብለዋል።

📱በተለይም በአሁኑ ወቅት የሚስተዋለው ያልተገደበ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም በሕጻናት አስተዳደግ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያመጣም ጠቁመዋል። ይህንን በመረዳት ለልጆች ደኅንነት እና መልካም አስተዳደግ ትኩረት እንዲሰጠውም ጥሪ አቅርበዋል።

በአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የአረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች እና የቤተሰብ ጉዳይ ዳይሬክተር መንበሩ የወርቅ እንደገለጹት የዘንድሮው በዓል በልጆች ደኅንነት ላይ ትኩረት በማድረግ በልጆች ላይ የሚደርሰውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ ያለመ ነው።

ጠንካራ ማኅበረሰብ ለመፍጠር መሰረቱ ቤተሰብ መኾኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ እየተስተዋሉ ላሉት ማኅበራዊ ቀውሶች ዋነኛው ምክንያት የቤተሰብ እሴቶች መሸርሸር እንደኾነ አስረድተዋል።

ችግሩን ለመፍታት አጋር እና ባለድርሻ አካላት በቤተሰብ አሥተዳደር ጉዳዮች ላይ በንቃት መሳተፍ እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ ወይዘሮ አበበች መልኬ እንደገለጹት የቤተሰብ በዓል መከበሩ መልካም የቤተሰብ እሴቶቻችንን ለማስቀጠል እና ጠንካራ ቤተሰብን ለመገንባት ፋይዳው የጎላ ነው።

👨‍👩‍👧‍👦✅ ጠንካራ ቤተሰብ ለመገንባት በተለይም ወላጆች በሕጻናት አስተዳደግ ላይ ልዩ ክትትል ሊያደርጉ እንደሚገባ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

#አሚኮ #የቤተሰብ ቀን #ኢትዮጵያ

#አሚኮ_ዜና #የቤተሰብ_በዓል #ባሕር_ዳር #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous article🗳️​በባሕር ዳር ከተማ የወጣቶች የጎዳና ላይ የምርጫ ቅስቀሳ ተካሄደ።
Next article“ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ ስኬቶችን በውጤት እናስቀጥላለን”