🗳️ “ክልሉ መንግሥት አልባ እንዲኾን አንፈልግም፤ ምርጫ ማድረግ መሠረታዊ ነው” የስማዳ ወረዳ ነዋሪዎች

5

 

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምርጫ እና የማኅበረሰብ ተሳትፎ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ የማይነጣጠሉ ገጽታዎች ናቸው። ምርጫ ትርጉም የሚኖረውም ማኅበረሰቡ በንቃት፣ በነጻነት እና በባለቤትነት ስሜት ሲሳተፍበት ነው።

ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉት የስማዳ ወረዳ ነዋሪ ወረዳው በተለያዩ ጊዜያቶች የጸጥታ ችግሮች የነበሩበት ቢኾንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተፈጠረ አንጻራዊ ሰላም የመራጮች ምዝገባ መከናወኑን ነግረውናል።

እርሳቸውም የምርጫ ካርድ ማውጣታቸውን እና የሚፈልጉትን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ገልጸውልናል።

ምርጫው ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ እና ጠንካራ መንግሥት እንዲመሠረት የሕግ የበላይነትን አክብሮ መንቀሳቀስ ተገቢ እንደኾነም አንስተዋል።

ሌላኛው የስማዳ ወረዳ ነዋሪ አሁን ላይ መረጋጋት እና አንጻራዊ ሰላም ተፈጥሮ የምርጫ ምዝገባ መደረጉን ገልጸውልናል። የምረጡኝ ቅስቀሳዎች እየተደረጉ እንደኾነም አንስተዋል።

ነዋሪው በወሰዱት ካርድ መሠረት ግንቦት 24/2018 ዓ.ም የሚፈልጉትን ፓርቲ ለመምረጥ በጉጉት እየጠበቁ መኾናቸውንም አጫውተውናል።

ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ደግሞ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች እያስተማሩ እንደኾነ ነው ያነሱት። እርሳቸውም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ነግረውናል።

“የሀገር እጣ ፈንታ የሚወሰነው በመንግሥት ምሥረታ ነው፤ “ክልሉ መንግሥት አልባ እንዲኾን አንፈልግም” ለዚህም ምርጫ ማድረግ ያስፈልጋል” ብለዋል።

#አሚኮ #ምርጫ_2018 #ኢትዮጵያ🇪🇹

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የግራንዴር ሴራሚክ ፋብሪካን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አደረጉ።
Next articleፋብሪካው በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ሽግግር ጉዞ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ ያመላከተ ነው።