ፋብሪካው በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ሽግግር ጉዞ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ ያመላከተ ነው።

11

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ)ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በሞጆ ከተማ የተገነባውን የግራንዴር ሴራሚክ ማምረቻ ፋብሪካን መርቀዋል።

‎በግራንዴር ሴራሚክ ማኑፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተገነባው ፋብሪካ መሰረት ልማቱ በ300ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ፣ የዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ የሴራሚክ እና የፖርሲሌን ንጣፎች ማምረቻ ፋብሪካ ነው ። ከዕቅድና መሬት ዝግጅት እስከ ሙሉ ሥራ ማስጀመር የወሰደው ጊዜ ዘጠኝ ወራት ብቻ ነው።

‎​በአሁኑ ወቅት 60×60 የሴራሚክ ንጣፎችን በስፋት ማምረት የጀመረው ይህ ፋብሪካ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ የምርት ዓይነቶቹን በማስፋት የ80×80፣ 60×120፣ 70×140 እና 80×160 መጠን ያላቸውን የንጣፍ ዓይነቶችን፣ የአውሮፓን የጥራት ደረጃ ያሟሉ የፖርሲሌን ምርቶችን ማቅረብ እንደሚጀምር ይጠበቃል።

ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ መዋዕለ ነዋይ የወጣበት ይህ ፋብሪካ፣ በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ሽግግር ጉዞ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ ያመላከተ ክንውን ነው።

‎ለ​ፋብሪካው ምርት የሚያስፈልጉት ጥሬ ዕቃዎች 80 በመቶ የሚኾነው ከፋብሪካው በ100 ኪሎ ሜትር ክበብ ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ይህም ሙሉ በሙሉ የተቀናጀ እና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር የተሳሰረ የአቅርቦት ሰንሰለት ፈጥሯል።

ኢትዮጵያ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት ባላፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ ከ4 ነጥብ 85 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማዳን በቻለችበት በዚህ ወቅት የግራንዴር ሴራሚክ መከፈት የውጭ ምርት ጥገኝነትን የሚቀንስ ብቻ ሳይኾን ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ እንድትኾን የሚያስችላት መኾኑን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous article🗳️ “ክልሉ መንግሥት አልባ እንዲኾን አንፈልግም፤ ምርጫ ማድረግ መሠረታዊ ነው” የስማዳ ወረዳ ነዋሪዎች
Next article“ቃላችንን ጠብቀን ዛሬን በአግባቡ እየሠራን፣ ነገንም አሰላስለን እየተለምን ነው” አቶ ፍስሐ ደሳለኝ