
ባሕር ዳር: ግንቦት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ስኬታማ ምርጫ የአንድ ሰሞን ኹነት ብቻ ሳይኾን የሀገርን ኅልውና፣ የሕዝብን ልእልና እና የኢኮኖሚ ጥንካሬን የሚወስን የረጅም ጊዜ የሀገር ስንቅ እንደኾነ ይታመናል።
የዘርፉ የፖለቲካ ሳይንስ ተንታኞች ሀገርን ወደ አስተማማኝ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማሸጋገር ንቁ የዜጎች ተሳትፎ የተረጋገጠበት ስኬታማ ምርጫ ማካሄድ ወሳኝ መኾኑንም ይናገራሉ።
የጅንካ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሣይንስ መምህር ምስክር ከተማ ፤ ምርጫ አንዳንዶች እንደሚሉት የሥልጣን ዕድሜ ማራዘሚያ ሳይኾን ዓላማው መንግሥት መመሥረት መኾኑን ተናግረዋል። ከነጉድለቱም ቢኾን ጊዜውን ጠብቆ ምርጫ ማካሄድ አስፈላጊ የሚኾነውም ለዚህ ነው ይላሉ።
በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሣይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ረዳት ፕሮፌሰር ዳምጠው ተሰማ እንደሚሉት ደግሞ የየትኛውም ሥርዓት ቀጣይነት በሕዝብ አመኔታ እና ተቀባይነት ላይ ይመሰረታል። ይህ አመኔታ የሚመጣውም ደግሞ በምርጫ ነው ይላሉ።
ስኬታማ ምርጫን ማካሄድ ለሀገር ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው ያሉት ምሁራኑ፤ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በ “ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ” አግባብ ማጠናቀቅ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጠቀሜታው ከፍተኛ እንደኾነም ተናግረዋል።
🇪🇹 ለመኾኑ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ኾኖ ሲጠናቀቅ ሀገር ምን ታተርፋለች ? ምሁራኑ ማብራሪያ አላቸው፦
📜 የተጀመረውን የተረጋጋ የፖለቲካ ባሕል ማስቀጠል ትችላለች፣
🕊️ የተረጋጋች፣ ሰላም እና ልማቷን ያረጋገጠች ሀገር የመገንባት ሂደቷን ታጠናክራለች፣
🌾በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በኢንዱስትሪ እና በሌሎች ዘርፎች ያላትን ሃብት ተጠቅማ የኢኮኖሚ ጥንካሬዋን እንድታረጋገጥ ያስችላታል፣
🏙️ ኢትዮጵያ ችግሮችን በንግግር የሚፈታ፣ በሀሳብ ልእልና የሚያምን፣
🗳 በካርድ ብቻ መንግሥትን የሚመሠርት ሥልጡን ሕዝብ እንዳላት ለዓለም ለማሳየት ገጽታዋን ትገነባለች፣
🗺️ ዓለም የኢትዮጵያ መንግሥት የሕዝብ አመኔታ ያለው መኾኑን እንዲረዳ ያደርጋል፣
🤝 የውጭ ዲፕሎማሲው የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥቅም እና ክብር የጠበቀ እንዲኾን ያስችላል።
🌍 ሌላው ዓለም ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆም የተሻለ ዕድልም ይፈጥርላታል፣
📈 የኢኮኖሚ፣ የባሕል፣ የቱሪዝም እና መሰል ሀብቶች በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ የተሻለ ገጽታ እንዲኖረው ያግዛል፣
💰 ዓለም አቀፍ የልማት እና የድጋፍ ግንኙነቶች እንዲሰፉ ዕድልም ይፈጥራል።
በጥቅሉ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሁሉም የሚበጀው ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ማድረግ ነው። ለወደፊት የኢትዮጵያ ዕድገት እና ብልጽግና መሠረት የሚጣልበት፤ ለሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር መሰረት እንዲኾንም የኹሉም ማኅበረሰብ አበርክቶ ያስፈልጋል ብለዋል የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራኖቹ።
ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ
#አሚኮ_ዜና #7ኛው_ምርጫ #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
