🇪🇹 “መንግሥት ምርጫውን 🗳️ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና አሳታፊ የማድረግ ድርብ ኀላፊነቱን እየተወጣ ነው” አቶ እድሜዓለም አንተነህ

6

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ግንቦት 24/2018 ዓ.ም ለሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃ እና ሕዝቡ ያለምንም ሥጋት የሚሳተፍበት እንዲኾን አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳደር አስታወቋል።

​የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ ዕድሜዓለም አንተነህ ለአሚኮ እንደገለጹት፤ የምርጫ ሂደቱ ሕግን መሠረት ያደረጉ በርካታ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል። መንግሥት ምርጫውን ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና አሳታፊ የማድረግ ድርብ ኀላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

​”የእኛ ትልቁ መመዘኛ የትኛው ፓርቲ ያሸንፋል የሚለው ሳይኾን ሕዝቡ በነፃነት እና ያለምንም ሥጋት የፈልገውን የሚመርጥበትን ዕድል ማረጋገጥ ነው” ብለዋል። በዚህም ሕዝቡ ይወክለኛል ለሚለው ፓርቲ ድምጽ መስጠት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በዞኑ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር የጋራ ምክር ቤት ተቋቁሞ በቅንጅት እየተሠራ መኾኑን ነው የገለጹት። ተፎካካሪ ፓርቲዎች ማኒፌስቶአቸውን እና አማራጭ ፖሊሲዎቻቸውን ለሕዝብ የሚያስተዋውቁበት እንዲሁም የምርጫ ቅስቀሳ የሚያደርጉበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም አንስተዋል።

ገዥው ፓርቲም ለመራጩ ሕዝብ የምርጫ ቅስቀሳ እና ማኒፌስቶ የማስተዋወቅ ሥራ በስፋት እያከናወነ መኾኑን ነው የተናገሩት።

​በዞኑ ካለው የማኅበረሰቡ ሰላም መሻሻል ጋር ተያይዞ የሕዝቡ የሰላም ስሜት እና ሥነ-ልቦና በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ዕድሜዓለም ይህም ለምርጫው ሰላም አይነተኛ ሚና እንደሚጫዎት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
​ሰላማዊ ምርጫ ለማካሄድ ከጸጥታ ኀይሎች ጋር በመቀናጀት ዝግጅት መደረጉንም አንስተዋል።

​የመራጮች ምዝገባ እና የፓርቲዎች ቅስቀሳ ሂደቶች የምርጫ ቦርድን መርሐ ግብር ጠብቀው እየተከናወኑ መኾኑንም አስረድተዋል።
ለምርጫው ስኬታማነት መሥራት ሀገራዊ ኀላፊነት መኾኑም ተመላክቷ።

ዘጋቢ፦ሥራውድንቅ ደሳለው

#አሚኮ_ዜና #7ኛው_ምርጫ #ምዕራብ_ጎጃም #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleከነዳጅ እጥረት እፎይታ እስከ አካባቢ ጥበቃ !
Next article“ሰላማዊ ምርጫ 🗳 አካሂዶ የኢትዮጵያን 🇪🇹 ሥልጡንነት ለዓለም ማሳየት ያስፈልጋል” የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን