
ባሕር ዳር: ግንቦት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአሁኑ ወቅት ታዳሽ ኃይል ላይ ትኩረት በመደረጉ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በብዛት ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው፡፡
ለዚህም የኤሌክትሪክ ባጃጆች መበራከት የትራንስፖርት ዘርፉ ከነዳጅ ጥገኝነት ወደ ታዳሽ ኃይል እየተሸጋገረ ስለመኾኑ ማሳያ ነው፡፡
ወጣት ኪሩቤል ቴዎድሮስ በባሕር ዳር ከተማ የኤሌክትሪክ ባጃጅ አሽከርካሪ ሲኾን ለሥራው ምቹ መኾኑን ነግሮናል፡፡ ከዚህ በፊት በቤንዚን የሚሠራ ባጃጅ ሲያሽከረክር መቆየቱን ያነሳው ወጣት ኪሩቤል ነዳጅ ለማግኘት እስከ ሦስት ቀናት ወረፋ ይጠብቅ እንደነበር አንስቷል፡፡
አሁን ላይ የኤሌክትሪክ ባጃጅ እያሽከረከረ ጊዜውንም፣ ገንዘቡንም መቆጠብ እንደቻለ ነው የገለጸው፡፡
“ቀን ሥሠራ ውየ ማታ ላይ ቻርጅ አደርጋለው፤ በማግስቱም ያለምንም ስጋት ሥራየን በአግባቡ እሠራለሁ ብሏል ወጣቱ፡፡ በነዳጅ የሚሠሩ ባጃጆች ላይ የሚያገኘውን ገንዘብ አብዛኛውን ለነዳጅ ወጭ ይውል እንደነበር ያነሳው ወጣት አሁን ላይ በቀን እስከ ሁለት ሺህ ብር ገቢ እንደሚያገኝም ገልጿል፡፡
በቤቱ ውስጥ ለኤሌክትሪክ ቻርጅ ማድረጊያ በወር እስከ 500 ብር ብቻ እንደሚያወጣ ነው የተናገረው፡፡ ቻርጅ ለማድረግም በየትኛውም ሶኬት መጠቀም ይቻላል ብሏል፡፡ ተገልጋዮቹም ደስተኛ መኾናቸውን ነው የገለጸው፡፡
ባጃጆቹ የኋላ ካሜራ ያላቸው በመኾኑ በእንቅስቃሴ ላይ አደጋ ለመቀነስም አስተዋጽኦ እንዳላቸው ተናግሯል፡፡ የኤሌክትሪክ ባጃጆች የሚለቁት ጋዝ ባለመኖሩ አካባቢን ከብክለትም ይታደጋሉ ነው ያለው፡፡
ባጃጁ በሚሽከረከርበት ጊዜ የሚረብሽ ድምጽ የለውም፤ ይህም ለተሳፋሪ ምቹ እና አካባቢንም ከድምጽ ብክለት ነጻ ያደርጋል ነው ያለው፡፡ ከተማው ላይ ቁጥራቸው እየጨመረ መምጣቱንም ገልጿል፡፡
በኤሌክትሪክ ባጃጅ አገልግሎት ሲጠቀም ያገኘነው ተገልጋይ አቶ ካሳው ወንዳለ የኤሌክትሪክ ባጃጆች በከተማው እየሰጡት ያለው አገልግሎት ጥሩ መኾኑን አንስተዋል፡፡ በተለይም የነዳጅ እጥረት በሚያጋጥምበት ጊዜ ማኅበረሰቡን ከእንግልት እንደሚታደጉት ነው የተናገሩት፡፡
የሚሰጡት አገልግሎት በመደበኛው ታሪፍ መሠረት ሲኾን በምቾት እና በቅልጥፍና አገልግሎት መስጠታቸው እንዳስደሰታቸውም ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
