“ብልጽግና ፓርቲ መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጡ ፖሊሲዎችን ዘርግቶ ሀገርን ለማሻገር እየሠራ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

7

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በባሕር ዳር ከተማ የሚገኙ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍል ተወካዮችን አወያይተዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት መንግሥት በተደጋጋሚ ሁሉንም የሰላም አማራጭ እየተጠቀመ መኾኑን ገልጸዋል።

አሁንም ቢኾን ሰላማዊ እና ሕጋዊ መንገድን ተከትሎ ለሚመጣ አካል መንግሥት በሩ ክፍት ነው ብለዋል። የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና እናቶች ወደ ጫካ የገቡትን ኃይሎች መምከር እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።

የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ዘመናዊ አሠራርን በመተግበር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ስለመኾኑም አንስተዋል።

“ብልጽግና ፓርቲ መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጡ ፖሊሲዎችን ዘርግቶ ሀገርን የሚያሻግሩ የልማት ሥራዎችን እየሠራ ስለመኾኑም” ጠቁመዋል።

ባሕር ዳር ከተማ ትልቅ የቱሪዝም መዳረሻ መኾኗን የገለጹት ርእሰ መሥተዳድሩ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ያስፈልጋሉ ነው ያሉት። ለዚህም ባለሃብቶች በስፋት ተሠማርተው ሊሠሩበት እንደሚገባ አንስተዋል።

የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሕዝቡ ድጋፍ እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል። የሚያጋጥሙ ችግሮችንም ደረጃ በደረጃ እንደሚፈቱ አረጋግጠዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የቀጣዩን የሀገራችንን ዕጣ ፈንታ የምንወስንበት ነው ብለዋል።

በዚህ ወቅት የባሕር ዳር ሕዝብ በታሪክ ዕድለኛ የኾነበት ነው ያሉት አቶ ጎሹ ለዚህም ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ታታሪ የኾኑ እጩዎች መቅረባቸውንም አብራርተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም በከተማዋ እየተሠሩ የሚገኙ የልማት ሥራዎችን እና ለወጣቶች እየፈጠሩት ያለውን የሥራ እድል አንስተው ምስጋና አቅርበዋል። በቀጣይም ከተማዋን የበለጠ በማስዋብ፣ ሰላምን በማረጋገጥ እና በሁሉም የልማት ሥራዎች ከመንግሥት ጎን ኾነው እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል። መጭው ምርጫም በስኬት እንዲጠናቀቅ ድምጽ ከመስጠትም ባሻገር ሰላምን ለማስጠበቅ በንቃት እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous article🗳️ “ሴቶች በድምጻቸው ሀገር ይገነባሉ ፤ በአንደበታቸው ሰላምን ይሰብካሉ”
Next article🗳️ 10 ቀናት ብቻ በቀሩት ምርጫ የሚበጅዎትን ለመምረጥ ምን ያህል ተዘጋጅተዋል ?