የኢትዮ- ዱባይ የኢንቨስትመንት አጋርነት መጀመር የሁለቱን ሀገራት የንግድ ልውውጥ እንዲያድግ አድርጎታል።

5

 

አዲስ አበባ: ግንቦት 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “አዲስ አድማስ” በሚል መሪ መልዕክት የተዘጋጀው የኢትዮ ዱባይ ኢንቨስትመንት ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በፎረሙ የዱባይ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያላቸውን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ ተጠቅመው መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈስሱ ጥሪ ቀርቧል።

ፎረሙ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች እና ኢትዮጵያ ያላቸውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት በማጠናከር የጋራ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ያስችላል ነው የተባለው።

የዱባይ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት እና ዋና ሥራ አሥፈፃሚ መሐመድ አሊ ረሺድ “የኢትዮ-ዱባይ ኢንቨስትመንት አጋርነት ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የንግድ ልወውጥ አድጓል” ብለዋል።

በዚህም በተለያዩ ዘርፎች የሚደረጉ የሁለትዮሽ የኢንቨስትመንት ግንኙነት እየጨመረ መምጣቱንም አንስተዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምሥራቅ እስያ እና ፓስፊክ ሀገራት ጉዳዮች ዳይሬክተር አምሃ ኀይለ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ከተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ጋር ያላት አጋርነት እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

በኢንቨስትመንት አጋርነታቸው ከ169 በላይ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በማዕድን፣ በሪልስቴት፣ በማኑፋክቸሪንግ እና ሌሎችም ዘርፎች እየተሳተፉ መኾኑን አንስተዋል።

በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች የኢትዮጵያ ባለሙሉሥልጣን አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ.ር) ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ዓመታት ለኢንቨስትመንት ምቹ ሪፎርሞችን በማድረጓ የውጭ አልሚዎች ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ የተማረ በቂ የሰው ኀይል፣ የመሠረተ ልማት፣ የአማራጭ ፓሊሲ እና የመንግሥት ቁርጠኝነት ያለባት ሀገር መኾኗ ደግሞ የኢንቨስትመንት የስበት ማዕከል አድርጓታልም ነው ያሉት አምባሳደሩ።

የኢትዮጵያ ንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አይናለም ዓባይነህ (ዶ.ር) ከዱባይ ንግድ ዘርፍ ማኅበራት ጋር በጋራ በተዘጋጀው ፎረም ከ20 በላይ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሀብቶች ተገኝተዋል ብለዋል።

በፎረሙ ላይ የተለያዩ አጋር እና ባለድርሻ አካላትን ጨምሮ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶችም ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ- ቤተልሄም ሰለሞን

#አሚኮ_ዜና #የኢትዮ_ዱባይ #የኢንቨስትመንት_አጋርነት #ኢትዮጵያ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleሀገራዊ ምክክሩ ልዩነቶቻችንን በውይይት እና በመግባባት ለመፍታት ጠቃሚ መድረክ ነው።
Next articleምርምር እና የዲጂታል ዘርፍ የቀጣይ የሚዲያዎች ትኩረቶች መኾን ይገባቸዋል።