ሀገራዊ ምክክሩ ልዩነቶቻችንን በውይይት እና በመግባባት ለመፍታት ጠቃሚ መድረክ ነው።

5

 

አዲስ አበባ: ግንቦት 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሃይማኖት አባቶች እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ያሳተፍ የሀገራዊ ምክክር አጀንዳዎች ማረጋገጫ ግብዓት ማሠባሠቢያ መርሐ ግብር አካሂዷል።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በኮሚሽኑ ባለፉት አራት ዓመታት የተሠሩ ሥራዎችን ገለጻ ያደረጉ ሲኾን በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች በ1ሺህ 234 ወረዳዎች አጀንዳ ማሠባሠብ መቻሉን ተናግረዋል።

ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ የሃይማኖት ተቋማት እና ሁሉም ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በተመረጡ አጀንዳዎች ላይ በጋራ የምንወያይበት መድረክ ነው ብለዋል ዋና ኮሚሽነሩ።

በቀጣይ በሚጠበቀው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤም 4ሺህ ተሳታፊዎችን እንደሚያሳትፍ ገልጸዋል::

የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክርቤት ፕሬዝዳንት አሕመድ ሁሴን (ዶ.ር) ሀገራችን በዚህ ወቅት ሰላም፣ ፍትሕ፣ እኩል ተሳትፎ እና ጠንካራ ተቋማት የምትፈልግበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች ብለዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ ልዩነቶቻችንን በውይይት እና በመግባባት ለመፍታት ጠቃሚ መድረክ ነው ሲሉም አንስተዋል።

መድረኩ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋርም እንደሚቀጥል ያነሱት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባየ ኦጋቶ (ዶ.ር) የተሠበሠቡ አጀንዳዎች ወደ ሕዝቡ ከመድረሳቸው በፊት የማረጋገጥ ሥራው ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ሚናው ከፍተኛ እንደኾነ አስረድተዋል።

ዘጋቢ፦ቴዎድሮስ ኃይለኢየሱስ

#አሚኮ_ዜና #ሀገራዊ_ምክክር #ኢትዮጵያ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleወጣቶች ለትልቅ ሀገራዊ ኀላፊነት መሥራት ይጠበቅባቸዋል።
Next articleየኢትዮ- ዱባይ የኢንቨስትመንት አጋርነት መጀመር የሁለቱን ሀገራት የንግድ ልውውጥ እንዲያድግ አድርጎታል።