
እንጅባራ: ግንቦት 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር የብልጽግና ፓርቲ አባላት እና ደጋፊ ወጣቶች በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለፓርቲው ያላቸውን ድጋፍ በጎዳና ላይ ሰልፍ ገልጸዋል።
“በጸና እና በተደራጀ የወጣቶች ተሳትፎ፤ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር እናሻግራለን” በሚል መሪ መልዕክት በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ከሁሉም የከተማ አሥተዳደሩ ቀበሌዎች የተውጣጡ ወጣቶች ተሳትፈዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዓለሙ ሰውነት ወጣቶች ሀገር ተረካቢ ብቻ ሳይኾኑ ሀገር ሠሪም መኾናቸውን ተገንዝበው ለትልቅ ሀገራዊ ኀላፊነት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
ብልጽግና ፓርቲ የወጣቶችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሰፋፊ ሀገራዊ ኢኒሼቲቮችን ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ መኾኑንም አንስተዋል።
ወጣቶች በቴክኖሎጂ የበለጸጉ፣ የነቁ እና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታን በውል የተረዱ ኾነው እንዲቀረጹ እየተሰጠ ያለው ነጻ የኮደርስ ሥልጠናም ፓርቲው ለወጣቶች የሰጠውን ትኩረት ማሳያ ነው ብለዋል።
ወጣቶች ለሀገር ግንባታ፣ ለዘላቂ ሰላም መጽናት እና ለልማት ያላቸውን አበርክቶ ከፍ ለማድረግ የሚያስችሉ ዕቅዶች ተነድፈው እየተሠሩ መኾኑንም አስረድተዋል።
እንደ ሀገር የተጀመረው የብልጽግና ጉዞ እውን እንዲኾን በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የወጣቶች ድምጽ ወሳኝ መኾኑንም አስገንዝበዋል።
የሰልፉ ተሳታፊዎችም ብልጽግና ፓርቲ የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ የሰጠው ትኩረት ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ገልጸዋል።
በፓርቲው መሪነት የተጀመሩ ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች እንዲሳኩ ከፓርቲው ጎን እንደሚቆሙም አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ሳሙኤል አማረ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
