
ደብረብርሃን፡ ግንቦት 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ብርሃን ከተማ በ82 ሚሊዮን ብር በጀት የተገነባው አዲስ ትምህርት ቤት ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ኾኗል።
ትምህርት ቤቱን ያስገነባው የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ በተገኘ በጀት ነው።
የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፋንታ ደጀን ፤ ግንባታው የትምህርት ፍትሐዊ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ታሳቢ አድርጎ የተከናወነ መኾኑን አብራርተዋል።
ትምህርት የወደፊት የሀገራችን ዋነኛው የዕድገት ተስፋ በመኾኑም ተፈናቃይ ሕጻናት በሚበዙበት አካባቢ ላይ ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።
በአማራ ክልል በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተሞች ልማት ዘርፍ አስተባባሪ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር) በበኩላቸው የክልሉ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት አብራርተዋል።
ፕሮጀክቱ የነገ ሀገር ተረካቢዎችን ለማፍራት እና የነዋሪዎችን የረጅም ጊዜ ጥያቄ ለመመለስ የተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ትምህርት ድህነትን የምናሸንፍበት ብቸኛው መሳሪያ መኾኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ግንባታው በአራት ወራት ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃቱም የከተማዋን የፕሮጀክት ማስፈጸም አቅም ማደግ የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በቀጣይም ከተማ አሥተዳደሩ ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶችን በማብዛት የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት በትጋት ይሠራል ነው ያሉት።
ትምህርት ቤቱ ስምንት መማሪያ ክፍሎች፣ ዘመናዊ ቤተ መጽሐፍት፣ የሳይንስ ቤተ ሙከራ እንዲሁም መጸዳጃ ቤቶችን ሙሉ በሙሉ አሟልቶ ተገንብቷል።
ለዚህ ትልቅ ትውልድ ተኮር ግንባታ የሚኾን ቦታን ያለምንም መሰሰት በነጻ የለገሱት የከተማዋ አርሶ አደሮችም ማኅበረሰባዊ ቁርጠኝነታቸውን በተግባር አሳይተዋል።
ዘጋቢ፦ለዓለም ለይኩን
#አሚኮ_ዜና #የትምህርትቤት_ግንባታ #ደብረ_ብርሃን #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
