
አዲስ አበባ: ግንቦት 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) መገናኛ ብዙኅን በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ዕለት እና ከምርጫ በኋላ የጋራ አቅማቸውን በማቀናጀት ፍትሐዊ የዘገባ ሽፋን እና ትክክለኛ መረጃን ለሕዝቡ ማድረስ እንደሚጠበቅባቸው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ ተናግረዋል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመገናኛ ብዙኅን የጋራ ስምሪትን በሚመለከት ከመገናኛ ብዙኅን ኀላፊዎች ጋር በአዲስ አበባ ከተማ ምክክር አድርጓል።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከዚህ በፊት ከነበሩት ምርጫዎች የተሻለ እንዲኾን የመገናኛ ብዙኅን ሥራዎች በቅንጅት እየተሠሩ ይገኛሉ።
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ መገናኛ ብዙኅን በምርጫ ሥራዎች ላይ በገለልተኝነት እና በሙያዊ ሥነ-ምግባር መሥራት እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
በምርጫ ወቅት ሀሰተኛ መረጃዎች በስፋት የሚሰራጩበት ዕድል ሰፊ በመኾኑ የመገናኛ ብዙኅን ተቋማት ሀቅን የማጣራት እና የማድረስ ሚናቸውን በልዩ ትኩረት መወጣት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
ምርጫው በሀገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ቀን የሚካሄድ በመኾኑ የሚዲያ ተቋማት በቅንጅት መሥራት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤታማ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ሰፊ ዝግጅት ማድረጋቸውን የተናገሩት በውይይት መድረኩ የተሳተፉ የመገናኛ ብዙኅን ኀላፊዎች የጋራ አቅምን በማቀናጀት እና ፍትሐዊ ሽፋንን በማጎልበት በተለያዩ ቋንቋዎች የምርጫውን ሂደት ለሕዝብ ተደራሽ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን አንስተዋል።
ዘጋቢ: ሰለሞን አሰፌ
#አሚኮ_ዜና #7ኛው_ምርጫ #መገናኛ_ብዙኅን #ኢትዮጵያ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
