
ባሕር ዳር: ግንቦት 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሊካሔድ 10 ቀናት ብቻ ቀርተውታል። ፖለቲካ ፓርቲዎችም የምርጫ ቅስቀሳቸውን ማካሄዳቸውን ቀጥለዋል።
ዜጎችም ግንቦት 24/2018 ዓ.ም ለነገይቱ ሀገር ዕድገት ወሳኝ የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ እየተጠባበቁ ይገኛሉ።
በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ፈንድቃ ከተማ አሥተዳደር ነዋሪ ሼህ ሱሌማን ዑመር በምርጫው ቀን ሚፈልጉትን ፓርቲ ለመምረጥ የሚያስችላቸውን ካርድ አውጥተው ቀኑን እየተጠባበቁ እንደሚገኙ ለአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ የሚገኘው ቅስቀሳ የሚመርጡትን ፓርቲ ለመለየት እንዳገዛቸው ነው የጠቆሙት።
በምርጫው ቀንም ወጥተው የሚፈልጉትን ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
በግጭት ሳይኾን በካርድ ሥልጣንን ማሻገር መለመድ አለበት ያሉት ሼህ ሱሌማን ነገ ሀገርን ሊያሳድግ የሚችለው በካርድ የሚደረግ ሽግግር መኾኑን ገልጸዋል። በግጭት ያደገ ሀገር የለም፤ በካርድ መምረጥ ደግሞ ለሀገር ይበጃል ነው ያሉት። ኹሉም አካል በካርድ የፈለገውን በመምረጥ የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲሰፍን ማድረግ እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።
ሌላኛው የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግምጃ ቤት ከተማ ነዋሪ አቶ አደራው ዘገዬ ካርድ ቀድመው በማውጣት የምርጫውን ቀን እየተጠባበቁ እንደኾነ ገልጸዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ነገ ለሀገር ይበጃል ያሉትን ኹሉ እያቀረቡ በመኾናቸው የሚፈልጉትን ለመምረጥ የሚያስችል በቂ ግንዛቤ እንዳገኙ ገልጸዋል።
በአካባቢያቸው ከሦሥት በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ እያካሄዱ መኾኑን የገለጹት አቶ አደራው የተሻለውን ለመምረጥ መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።
ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ የራሳቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ሰለሞን ስንታየሁ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
