ጀጎልን አሳምሮ የቱሪስት ፍስሰትን የጨመረው የኮሪደር ልማት።

4
ባሕር ዳር: ግንቦት 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሀረሪ ክልል ባለፉት ዓመታት በጀጎል ዓለም አቀፍ ቅርስ ከ22 ኪሎ ሜትር በላይ የኮሪደር ልማት ሥራ መከናወኑን የክልሉ ባሕል፣ ቅርስ እና ቱሪዝም ቢሮ ገልጿል።
በክልሉ ባሕል፣ ቅርስ እና ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ዳይሬክተር ኢንጅነር አሚር ረመዳን ባለፉት ዓመታት በጀጎል ዓለም አቀፍ ቅርስ ውስጥ ስለተከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎች በሚመለከት መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በክልሉ ባለፉት ዓመታት ቅርሶችን በማልማት እና በመንከባከብ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም በማሳደግ ረገድ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ሢሠሩ ቆይተዋል ነው ያሉት።
ከተከናወኑ ተግባራት መካከልም ታሪካዊ እና ጥንታዊ ቅርሶችን ለጎብኝዎች ምቹ እና ማራኪ ለማድረግ የተከናወኑ ውጤታማ ሥራዎች ለአብነት እንደሚጠቀሱ ተናግረዋል።
በክልሉ የሚገኙ ቅርሶችን በመንከባከብ እና በማልማት ረገድ የተከናወኑ ሥራዎችም የሐረርን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ያሳደጉ እና የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪስቶች ፍሰት እና ገቢ እንዲጨምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ስለመኾናቸው ጠቁመዋል።
በርእሰ መሥተዳድሩ ኦርዲን በድሪ ሀሳብ አመንጭነት በተደመረ አቅም እና በላቀ ቁርጠኝነት፤ ሕዝብን በማሳተፍ ከመንግሥት ምንም አይነት በጀት ሳይመደብለት ከ22 ኪሎ ሜትር በላይ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ማልማት መቻሉንም ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም 6ሺህ 114 ካሬ ሜትር የሚሸፍነው የጀጎል ግንብ ዙሪያም መልሶ የማልማት እና የአረንጓዴ ስፍራ እውን ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በዚህም ከ7 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩንም ነው ኢንጂነር አሚር የተናገሩት አካባቢያዊ ሀብት እና ዕውቀትን በመጠቀም በተከናወኑ ሥራዎች እውን የተደረገው ሥራም የቅርሱን ይዘት እና ታሪካዊነት ውብ እንዲኾን ማድረግ ስለመቻሉም ገልጸዋል።
በተከናወነው ሥራም በገጠር እና ከተማ የሚገኘው ሕዝብ እና ተቋማት እንዲሁም ማኅበራት እና የዲያስፖራ አባላት በኔነት ስሜት ተሳታፊ ስለመኾናቸውም አስረድተዋል።
በጀጎል መልሶ ማልማት የተሠሩ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ከተማዋ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ እንድትኾን ከማሳደግ ባለፈ ለነዋሪዎቹ የተመቸች እንድትኾን ያስቻለ መኾኑንም ጠቅሰዋል። በቀጣይም በጀጎል ዓለም አቀፍ ቅርስ ጥበቃ እና እንክብካቤ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous article“ድምጽን በነጻነት የመስጠት ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን” የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን
Next articleየፕላስቲክ ከረጢቶችን ባለመጠቀም ጽዱ ከባቢን እንፍጠር!