“ድምጽን በነጻነት የመስጠት ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን” የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን

3
🗳️
ባሕር ዳር: ግንቦት 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ግንቦት 24/2018 ዓ.ም የሚካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ እና አሳታፊ በኾነ መልኩ እንዲጠናቀቅ ሰፊ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የደቡብ ወሎ ዞን አስታውቋል።
​የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን የምርጫውን ስኬታማነት ለማረጋገጥ ሕዝቡን ያሳተፉ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
​በዝግጅት ምዕራፍ መራጩ ሕዝብ በምርጫው ላይ የበኩሉን አሻራ ማሳረፍ እንዲችል ሰፊ የንቃተ ህሊና ማሳደጊያ ሥራዎች መከናወናቸውን ነው የተናገሩት።
ሕዝቡ የዴሞክራሲያዊ መብቱ ባለቤት እንዲኾን እና ድምጹን በነጻነት “ይመራኛል” ለሚለው ፓርቲ እንዲሰጥ ለማስቻል ጥረት እንደተደረገ ነው የተናገሩት።
የምርጫው ሂደት ፍጹም ሰላማዊ እና ተዓማኒ እንዲኾን ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በዞን ደረጃ የጋራ ምክር ቤት ተቋቁሞ በቅንጅት እየተሠራ መኾኑንም ነው ዋና አሥተዳዳሪው የገለጹት።
ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ያለምንም ገደብ በነጻነት የምርጫ ቅስቀሳቸውን እንዲያደርጉ እና ማኒፌስቷቸውን ለሕዝብ እንዲያስተዋውቁ ምቹ ዕድሎች መፈጠራቸውን አንስተዋል።
“ድምጽን በነጻነት የመስጠት ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን” ነው ያሉት አሥተዳዳሪው።
ማኅበረሰቡ ድምጹን በነጻነት ከመስጠት ባለፈ እስከ ፍጻሜው ድረስ የድርሻውን እና ታሪካዊ ኀላፊነቱን እንዲወጣም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleከአራት ዓመት ጨለማ በኋላ ብርሃን ያገኘችው የሻሁራ ከተማ።
Next articleጀጎልን አሳምሮ የቱሪስት ፍስሰትን የጨመረው የኮሪደር ልማት።