
ባሕር ዳር: ግንቦት 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአለፋ ወረዳ ሻሁራ ከተማ ላለፉት አራት ዓመታት የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቋረጡ የነዋሪዎችን ሕይወት በእጅጉ ፈትኖ ቆይቷል።
የከተማው ነዋሪ አቶ ካሴ ይስማው፣ መብራት ጠፍቶ በነበረባቸው ዓመታት ማኅበረሰቡ የገጠመውን እንግልት ያስታውሳሉ። ችግሩ እንዲፈታላቸውም ከጓደኞቻቸው ጋር በመኾን መፍትሄ ፍለጋ ከክልሉ ርዕሰ መዲና ባሕር ዳር እስከ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ድረስ ሰባት ጊዜ መመላለሳቸውን ይናገራሉ።
በኤሌክትሪክ ኀይል እጦት ምክንያት በከተማዋ የነበረው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ተገትቶ እንደነበርም አቶ ካሴ ያስረዳሉ። በተለይም በማኑፋክቸሪንግ፣ በሆቴል፣ በወፍጮ እና በፀጉር ሥራ ዘርፍ የተሰማሩ በርካታ ነዋሪዎች ሥራቸውን አቁመው አካባቢውን ለቀው ለመሰደድ ተገድደዋል።
የመብራት መጥፋት ያስከተለው ሌላው መዘዝ የንጹህ መጠጥ ውኃ መቋረጥ ነው። ሌላኛው ነዋሪ አቶ ብርሃኑ ደሴ እንደሚሉት ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በከተማዋ ውኃ በመጥፋቱ ነዋሪው ለከፍተኛ እንግልት ተዳርጎ ቆይቷል።
“አንድ ጀሪካን ውኃ ለማግኘት ከሦሥት ሰዓት በላይ በእግር ተጉዘን በጋሪ እናመጣ ነበር፤ ንጹህ ውኃ በማጣታችንም ለውኃ ወለድ በሽታዎች ተጋልጠን ቆይተናል” ይላሉ አቶ ብርሃኑ።
አንድ ኪሎ እህል ለማስፈጨት እና አንድ ጀሪካን ውኃ ለመግዛት ብቻ እስከ 40 ብር ድረስ ለማውጣት ይገደዱ እንደነበርም ነዋሪዎቹ ያስታውሳሉ።
ዛሬ ላይ ግን ያ የጨለማ ጊዜ አብቅቶ ከተማዋ ዳግም በብርሃን ደምቃለች።
በትራንስፎርመር ብልሽት እና የቴክኒክ ችግር ምክንያት የኤሌክትሪክ አገልግሎቱ ለ4 ተከታታይ ዓመታት ያህል ተቋርጦ መቆየቱን የሻሁራ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ንጋቱ ጨቅሌ ተናግረዋል።
በዚህም የወረዳው ማኅበረሰብ እና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለአልተፈለገ ወጭ እና እንግልት መዳረጋቸውን እና ትልቅ የመልካም አሥተዳደር ጥያቄ ኾኖ መቆየቱን አንስተዋል።
ይሁን እንጅ አሁን ላይ ከፌዴራል እስከ ወረዳ ባሉ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ርብርብ ብልሽቱ ጥገና ተደርጎለት አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ነው ከንቲባው ያነሱት።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
