
ባሕር ዳር: ግንቦት 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የዴሞክራሲ ግንባታም ሆነ የሀገር ሁለንተናዊ እድገት ያለ ሴቶች ተሳትፎ ሙሉ ሊሆን አይችልም። ሴቶች ከሚሳተፉባቸው የፖለቲካ መድረኮች አንዱ ምርጫ ነው። ሴቶች ግንቦት 24 ለሚደረገው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ።
የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዋ ሰናይት ጸጋዬ የዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም የመራጭነት ካርዷን ቀድመው ካወጡት ሴቶች መካከል አንዷ ናቸው።
ምርጫ የሴቶችን መብትና ተጠቃሚነት ለማስከበር ትልቅ መሣሪያ መሆኑን የምታምነው ሰናይት “ለሴቶች መብት ጥብቅና የሚቆምና የተሻለ አማራጭ ይዞ የመጣን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅቻለሁ” ስትል የነቃ ተሳትፎዋን ትገልጻለች።
ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ ገነት መስፍንም በተመሳሳይ የምርጫን ጥቅም በመረዳት ካርዷን በቀዳሚነት ወስዳለች።
ምርጫ ሴቶች ድምፅ የመስጠት ብቻ ሳይሆን ወደ መሪነት የመምጫ መድረክ መሆኑን የምታነሳው ገነት ሂደቱ ሰላማዊና ፍትሐዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻዋን እየተወጣች መሆኑንም ትናገራለች።
እነዚህ እናቶች ግንቦት 24 በንቃት እየጠበቁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
የአብክመ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዝና ጌታቸው እንደገለጹት በክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲሰፍን የሴቶች የምርጫ ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ሴቶች በአደረጃጀት ተዋቅረው ካርድ እንዲያወጡ ሰፊ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል።
በዚህም በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የክልሉ ሴቶች በልዩ ሁኔታ በንቃት እየተሳተፉ መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል ነው ያሉት ምክትል ኃላፊዋ።
ተሳትፎው ከመራጭነት ባለፈ በዕጩነት፣ በተመራጭነት እና በታዛቢነት ጭምር መሆኑንም ጠቁመዋል።
“ካርድ ማውጣት ብቻውን ግብ አይደለም” የሚሉት ምክትል ኀላፊዋ ሴቶች በቀጣይም ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸውን ሊያረጋግጥላቸው የሚችለውን ፓርቲ በካርዳቸው ሊመርጡ ይገባል ብለዋል።
ምርጫው ሰላማዊ፣ ነጻና ፍትሐዊ እንዲሆን ሴቶች እያደረጉት ያለውን ሁለገብ አስተዋጽዖ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
