
ባሕር ዳር: ግንቦት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገር አቀፍ ደረጃ የፕላስቲክ ከረጢት ማምረት፣ ወደ ሀገር ማስገባት፣ መሸጥ እና መጠቀምን በተመለከተ የሚደነግግ አዋጅ ቁጥር 1383/2017 ጸድቆ ወደ ሥራ መግባቱ የሚታወስ ነው።
አዋጁን መሠረት በማድረግ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደርም ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚያገለግሉ የፕላስቲክ ከረጢቶችን መጠቀም ከመጋቢት 2018 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ጀምሮ ክልከላ ማድረጉ ይታወቃል።
በከተማ አሥተዳደሩ የአካባቢ ጥበቃ፣ ጽዳት እና ውበት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጽጌሬዳ አበበ ክልከላው ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ሢሠሩ መቆየቱን አንስተዋል።
በከተማዋ ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚያገለግሉ የፕላስቲክ ከረጢቶችን ሲጠቀም ወይም ሲያቀርብ የተገኘን አካል በአዋጁ በተደነገገው መሠረት ተጠያቂ ለማድረግ ሢሠራ መቆየቱንም ገልጸዋል። አሁን ላይ ክልከላውን ተላልፈው በተገኙ አምስት የፕላስቲክ አምራች ድርጅቶች ላይ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ነው የተናገሩት።
የፕላስቲክ ምርት ለረጅም ጊዜ የማይበሰብስ በመኾኑ በብዝኀ ሕይወት፣ በሰው እና በእንስሳት ጤና ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያመጣም ተናግረዋል። በተለይም በከተማ ካሉት የደረቅ ቆሻሻ ምጣኔ የፕላስቲክ ውጤቶች ከፍተኛውን መጠን እንደሚይዙም ጠቁመዋል።
ተግባራዊ መደረግ የተጀመረው ውሳኔም ከተማዋን ጽዱ እና ውብ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አመላክተዋል።
ማኅበረሰቡ ጉዳቱን ተገንዝቦ ከፕላስቲክ ከረጢት ይልቅ በቀላሉ የሚበሰብሱ ምርቶችን እንዲጠቀምም መክረዋል።
በከተማዋ ቅጣቱን ወዲያውኑ ከመተግበር ይልቅ ማስጠንቀቂያ ይቅደም በሚል ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ነው የተናገሩት። ወደፊት ግን ፕላስቲክን የሚተካ ምርት እንዲመረት ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ባለፈ የወጣው የሕግ ቅጣት እንደሚከበር ነው የጠቆሙት።
በአዋጁ አንቀጽ 25 ስር እንደተደነገገው አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል የፕላስቲክ ከረጢት ይዞ የተገኘ ማንኛውም ሰው ከ2 ሺህ እስከ 5 ሺህ ብር ይቀጣል ብለዋል፡፡ ይህንን በመገንዘብም ማንኛውም ሰው በተከለከሉ የፕላስቲክ ምርቶችን ከመገልገል መቆጠብ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የፕላስቲክ ከረጢት ያመረተ፣ ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባ፣ ለገበያ ያቀረበ ወይም ሲሸጥ የተገኘ ከ50 ሺህ ብር እስከ 200 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲኹም ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ያስቀጣል፡፡
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
