
ባሕር ዳር: ግንቦት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ከሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ጋር ተያይዞ ከከተማ እና ማኅበራዊ ክላስተር የመንግሥት ሠራተኞች ጋር የተለያዩ የውይይት መድረኮችን አካሂዷል።
የማኅበራዊ ክላስተር የመንግሥት ሠራተኞች መድረክ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኀላፊ ባንቺአምላክ ገብረ ማርያም ኢትዮጵያ ላለፉ አምስት ዓመታት ትልልቅ ሥራዎች ስትሠራ ብትቆይም የተለያዩ ችግሮች ገጥመዋት እንደነበር አስታውሰዋል። በማሳያነትም አማራ ክልል ባለ የጸጥታ ኹኔታ የትምህርት እና የጤና ዘርፉ የገጠሙትን ችግሮች ጠቅሰዋል።
ፈተናዎችን ወደ ድል ለመቀየር በተሠሩ ሰፊ የልማት ሥራዎች ግን ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል። ክልሉ ከልማት ባሻገር ለሰላም ጉዳይ ሰፊ ትኩረት መስጠቱንም ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ትናንትናን እና ዛሬን አክማ ነገን ለመሥራት በምታደርገው ርብርብ መንግሥት ሠራተኞች የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ቀላል አለመኾኑንም ገልጸዋል። ብልጽግና ፓርቲ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ቢመረጥ ከዚህ በፊት የተጀመሩ የልማት እና መልካም አሥተዳደር ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመላክተዋል።
የከተማ የመንግሥት ሠራተኞች መድረክ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ባሕል ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ መስፍን አበጀ (ዶ.ር) የተካሄደው ውይይት ምሁራን ከወቅታዊ ጉዳይ በመነሳት በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሊኖራቸው የሚገባ ሚና ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ መኾኑን ተናግረዋል።
በመድረኩ ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት የሠራቸው ሥራዎች እና ቀጣይ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ቢመረጥ ሊሠራቸው ያሰባቸው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የመድረኩ ተሳታፊ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የትምህርት ሚዲያ ዳይሬክተር ዳንኤል ሰብስቤ በተፈጠረላቸው ግንዛቤ ክልሉ እና ሀገሪቱ ያሉበትን ኹኔታ በጥልቀት መረዳታቸውን ገልጸዋል። በዚህም በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጁ መኾናቸውን ነው የነገሩን።
የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ የሥርዓተ ጾታ ባለሙያ ጸጋየ አየለ ደግሞ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሐዊ እንዲኾን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
