ሰላም የሚረጋገጠው በሁሉም አዎንታዊ ተሳትፎ ነው።

6
ጎንደር: ግንቦት 13/2018 ዓ .ም ( አሚኮ) ‎የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን በጎንደር ከተማ ጠዳ የሥልጠና ማዕከል የሰላምን አማራጭ ለተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች የተሃድሶ ሥልጠና መሥጠት ጀምሯል ።
‎በመርሃ ግብሩ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ ጨምሮ ከፍተኛ የፌደራል እና የክልል የሥራ ኃላፊዎች ፣ የጦር መኮንኖች ፣ የሰላምን አማራጭ ቀደም ብለው የተቀበሉና በቅርብ የገቡ የቀድሞ ታጣቂዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
‎መርሀ ግብሩን በንግግር የከፈቱት የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን ሰላምን መርጠው ለመጡ የቀድሞ ታጣቂዎች ምስጋና አቅርበዋል።
‎ወጣቶች ከሥልጠናው በኋላ ንቁ ማኅበራዊ ተሳታፊ እንዲሆኑም ጠይቀዋል።
‎እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ እስካሁን በሀገሪቱ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ከ88 ሽህ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች ሥልጠና የመሥጠትና መልሶ የማቋቋም ተግባር መከናወኑን ጠቅሰዋል።
‎አሁንም በተጥቅ ትግል ያሉ ወጣቶች የሰላም አማራጭ እንዲቀበሉ ጠይቀዋል።
‎የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ በሪሁን መንግስቱ በበኩላቸው ሰላም በመወያየትና በመደማመጥ ማረጋገጥ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
‎ውይይቱም በጋራ መሥራትን ፣ መተጋገዝን እና አብሮነትን ለማስገንዘብ መኾኑን አስገንዝበዋል።
‎የሰላም ጉዞ በአንድ አካል ብቻ የሚስተካከል ባለመሆኑ በጋራ ልንስራ ይገባልም ነው ያሉት።
‎መገዳደል ሊቆም እንደሚገባ መልዕክት ያስተላለፉት ደግሞ የጎንደር አካባቢ መከላከያ አዛዥ ብርጋዴል ጀኔራል መለስ በለጠ ናቸው።
‎ለዘላቂ ሰላም በጋራ ለመስራት ዝግጁ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
‎በአማራ ክልል ከ30 ሽህ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭ ተቀብለዋል ያሉት በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአሥስተዳደር ጉዳዮች ዘርፍ አሥተባባሪ አማኑኤል ፈረደ(ዶ/ር) እስካሁን ከ15 ሽህ በላዩ ሥልጠና መውሰዳቸውን ገልጸዋል።
‎ችግሮችን በነፍጥ ሳይሆን በንግግር እና ውይይት መፍታት ባሕል ማድረግ እንደሚገባም አንስተዋል።
‎ተደራጅተው ወደ ስራ መግባት ለሚፈልጉ ወጣቶች በክህሎታቸው ሥራ እንዲጀምሩ ተደርጓል ያሉት አስተባባሪዉ ቀሪዎችንም ወደሥራ ለማስገባት እየተሰራ ነው ብለዋል።
‎በሥልጠናው ያነጋገርናቸው ወጣቶች በበኩላቸው ሰላም የሁለም ነገር መሰረት በመኾኑ ለዘላቂ ሰላም በትኩረት እንደሚሰሩ ነግረውናል።
‎ከሥልጠናው በኋላ በማኅበራዊ አገልግሎቶች ለመሳተፍ ቁርጠኛ መኾናቸውንም አንስተዋል።
‎በትጥቅ ትግል የሚንቀሳቀሱ ወጣቶች የሰላም አማራጭ እንዲቀበሉ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- አዲስ አለማየሁ
Previous article“ብልጽግና ሴቶች እና ወጣቶች አቅማቸውን እንዲጠቀሙ አድርጓል” የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንታይቱ ካሴ
Next articleኢትዮጵያ ትናንትናን እና ዛሬን አክማ ነገን ለመሥራት ርብርብ እያደረገች ነው።