
ወልድያ: ግንቦት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የወልዲያ ከተማ ሴቶች ለብልጽግና ፓርቲ ያላቸውን ድጋፍ በአደባባይ ሰልፍ ገልጸዋል። “በጸና እና በተደራጀ የሴቶች ድምጽ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር እናሻግራለን!” በሚል መሪ መልዕክት ነው ሰልፉን ያካሄዱት።
የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ ወልድያን ዘመናዊ ከተማ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ከተማዋን ለማዘመን የሴቶች ድርሻ ጉልህ በመኾኑ ሁለንተናዊ ተሳትፏቸውን እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
ከተማ አሥተዳደሩም የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተደራጀ መንገድ ወደ ሥራ እንዲገቡ እየተሠራ ነው ብለዋል። ወደፊትም አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት።
የሴቶችን አቅም ማጎልበት ቤተሰብን መገንባት፣ ማኅበረሰብን ማነጽ እና ሀገርን ማሻገር ነው ያሉት ከንቲባ ዱባለ ፓርቲያቸው ለሴቶች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራቱን ይቀጥላል ብለዋል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል መንገድ ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ ቢሮ ኀላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ.ር) ብልጽግና ፓርቲ ሴቶችን ወደፊት በማምጣት ተሳትፏቸውን በተግባር ያረጋገጠ መኾኑን ገልጸዋል።
የወልድያ ከተማ ሕዝብ ለዓመታት ያነሳው የነበረን የአስፋልት መንገድ ምላሽ የሰጠው ብልጽግና ፓርቲ ነው ብለዋል። በኮሪደር ልማት እና ሕዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሌሎች ልማቶችንም ማከናወኑን አንስተዋል።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
