
ባሕር ዳር: ግንቦት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት “ኢትዮጵያ ወደ ተምሳሌት ሀገር” በሚል መሪ መልዕክት ለአማራ ክልል የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሠራተኞች ማኒፌስቶውን፣ እጩዎቹን የማስተዋወቅ እና የምረጡኝ ቅስቀሳ አካሂዷል።
ምርጫው ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ የልማት ድርጅት ሠራተኞች ስለሚኖራቸው ሚናም ውይይት ተደርጓል።
የአማራ ልህቀት ዲዛይን እና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ አብርሃም አያሌው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ትናንትን የምናክምበት፤ ለነገ መሠረት የምንጥልበት ትላልቅ ሀገራዊ ራዕይ እና እሳቤ ይዞ የሚካሄድ ምርጫ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል የመንግሥት የልማት ድርጅት ሠራተኞችም የነገን ታላቅ ዕድገት እና ብልጽግና ዕውን ለማድረግ የድርሻቸውን መወጣት ይገባቸዋል ነው ያሉት።
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በልማት ሥራቸው ውጤታማ እንዲኾኑ በሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ጠንካራ መንግሥት ለመመሥረት መዘጋጀት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ቅቡልነት ያለው ሥርዓት እንዲመሠረት ባለቤት ኾነው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
የመደመር መንግሥት በኹሉም ዘርፍ የሕዝብን ክብር እና ልዕልና የሚያስጠብቁ፤ ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጡ እና አፍሪካዊት ኀያል ኢትዮጵያን ለመገንባት የለውጥ ሥራዎችን እያከናወነ መኾኑን አስረድተዋል።
በሥራውም ውጤት እያመጣ ነው ብለዋል። ሠራተኞችም ይህን ተገንዝበው መምረጥ አለባቸው ነው ያሉት።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በክልሉ እና በሀገር ደረጃ በተፈጠሩ የሰላም እጦቶች የልማት ድርጅት ሠራተኞች ተጎጂ መኾናቸውን አንስተዋል።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት በመሳተፍ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ እና ሰላም እንዲሰፍን ለመሥራት ዝግጁ መኾናቸውን አረጋግጠዋል።
ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲደረግ የኹሉንም የማኅበረሰብ ክፍል የጋራ ጥረት የሚጠይቅ በመኾኑ ኹሉም መብቱን ለመጠቀም እና ሰላምን ለማስፈን መሠራት አለበትም ብለዋል።
ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
