
ባሕር ዳር: ግንቦት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦ ወረዳ የምርጫ ቅስቀሳ አካሂደዋል። የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን ብልጽግናን መምረጥ አንድነትን፣ ሰላምን እና ዴሞክራሲን መምረጥ ነው ብለዋል።
ሕዝቡ ብልጽግናን በነቂስ ወጥቶ በመደገፉም አመሥግነዋል። ሕጋዊ እና ሕዝባዊ መንግሥት ለመመሥረት ብልጽግናን እንዲመርጡም አሳስበዋል።
በቅስቀሳው ላይ የተገኙት ሉባባ ኢብራሂም ብልጽግና ኅብረ ብሔራዊነትን፣ የጋራ ትርክትን እና አብሮነትን ለማጽናት የሚሠራ ፓርቲ ነው ብለዋል።
ፓርቲው የሕዝብን ጥቅም በማረጋገጥ ለሀገር ዕድገት እየሠራ መኾኑንም አንስተዋል። የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ወረባቦ ወረዳ የልማት ትንሳኤ ላይ ነው ብለዋል።
በወረዳው ግማሽ ቢሊዮን ብር ወጭ የተደረገባቸው የተለያዩ መሠረተ ልማቶች መገንባታቸውንም ተናግረዋል። ብልጽግና ፓርቲ የአካባቢውን ልማት እያረጋገጠ በመኾኑ ብልጽግናን እንዲመርጡም ጠይቀዋል።
ብልጽግና ትናንትን ከዛሬ እና ዛሬን ከነገ በማስተሳሰር ለትውልድ የሚሠራ ፓርቲ ነው ብለዋል። ወጣቶች የነገ የሀገር ተስፋዎች በመኾናችሁ የትናንት ቁስሎችን እያረመ እና እያስተካከለ ያለውን ፓርቲ በመምረጥ የነገ ሀገር ተረካቢነታችሁን ልታረጋግጡ ይገባል ብለዋል።
ለቀጣይ የሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት እና ለዘላቂ ልማት ብልጽግናን መምረጥ እንደሚገባም አሳስበዋል። ሴቶች የሀገር መሠረት ናችሁ ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ብልጽግና የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሠራ በመኾኑ ብልጽግናን ልትመርጡ ይገባል ብለዋል።
ብልጽግና የሃሳብ ልዩነትን የኅብረ ብሔራዊነት አካል አድርጎ እየሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል።
“በብልጽግና የማይፈታ ችግር የለም” ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ማኅበረተሰቡ አንድነቱን በማጠናከር ሰላሙን እንዲያጸና አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
