
አዲስ አበባ: ግንቦት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በደቡብ አፍሪካ ከተነሳውን “መጤ ጠል” የዜጎች ጥቃት የራሷን ዜጎች ለመጠበቅ በደቡብ አፍሪካ ኤምባሲዋ በኩል ስታደርግ ከነበረው እንቅስቃሴ በተጨማሪ በኢትዮጵያ የሚገኘውን የሀገሪቱን አምባሳደር ጠርታ ማነጋገሯን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞትዮስ (ዶ.ር) የደቡብ አፍሪካ የውጭ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ሮናልድ ሌሞንን ያነጋገሩ ሲኾን ሚኒስትሩ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በአጥቂዎች ላይ ማጣራት እያደረገ መኾኑን እና እርምጃ እንደሚወስድም ለኢትዮጵያ አቻቸው ገልጸውላቸዋል ተብሏል።
ኢትዮጵያ በአስተማማኝ መልኩ ለዜጎቿ ጥበቃ ለማድረግ በቅርቡ ወደ ደቡብ አፍሪካ ልዑክ ለመላክ መሰናዳቷንም ቃል አቀባዩ አሳውቀዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ ከሀገሪቱ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢንጅነር ዋሊድ ኤልኬረጅን ጋር ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ መክረዋል ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ዘጋቢ: አንዷለም መናን
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
