
አዲስ አበባ: ግንቦት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው በሰጡት መግለጫ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ.ር) ከአሜሪካ አቻቸው ማርክ ሩቢዮ ጋር መምከራቸውን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር በዋሽንግተን መዋቅራዊ ስምምነት ማድረጓንም በመግለጫቸው አንስተዋል።
ከ120 ዓመታት በላይ የቆየውን የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር በየዓመቱ ጉባኤ ይከናወናልም ብለዋል።
ስምምነቱ በዋናነት የኢኮኖሚ፣ የኢንቨስትመንት፣ የመከላከያ እና የደኅንነት ተቋማትን ለማጠናከር እንዲሁም ቀጣናዊ ሰላም እና መረጋጋትን ለማምጣት ዓላማ ያደረገ መኾኑም ተጠቅሷል ።
በተጨማሪ ኢትዮጵያ የተመድ 80ኛ ዓመትን በማክበር ባለብዙ ዘርፍ ዲፕሎማሲን አጠናክራ ለመቀጠል ቁርጠኛ መኾኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ለባለብዙ ዘርፍ ዲፕሎማሲ ያላትን ሚና የሚገልጹ አራት ቴምብሮችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከአንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጋር በመመረቅ ለ191 ሀገራት መሠራጨቱም ተገልጿል።
በብሪክስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሥብሠባ የተሳተፈችው ኢትዮጵያ፣ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚከሰቱ ግጭቶች በወቅቱ እልባት ካልተሠጣቸው በድንበር ብቻ ተወስነው እንደማይቀሩ መግለጿን ቃል አቀባዩ አሳውቀዋል።
ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
