“የሀገርን ሰላም እና አንድነት ለማስጠበቅ ሁሉም ሊተጋ ይገባል” የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ

8
አዲስ አበባ: ግንቦት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ሀገር አቀፍ የአደባባይ የምልጃ እና የጸሎት መርሐ ግብር ግንቦት 16/2018 ዓ.ም ሊያካሂድ መኾኑን ገልጿል። ይህንን ሁነት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የጉባዔው ዋና ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንደ ሀገር የሚከሰቱ ግጭቶችን እልባት ለመስጠት የሃይማኖት አባቶች ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
ይህንን ሚናቸውን ለመወጣት ጉባዔው ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች የሚሳተፉበትን ሀገር አቀፍ የአደባባይ የፀሎት መርሐ ግብር ለማካሄድ ወስኗልም ነው ያሉት።
የፊታችን እሁድ የሚካሄደው የጸሎት መርሐ ግብር የሀገሪቱን ሰላም ለማጽናት፤ የልማት ሥራዎችን ማኅበረሰቡ እንዲደግፍ ለማስቻል እንዲሁም የሰላም እና የአብሮነት መልዕክቶችን ለማስተላለፍ ያለመ ነው ብለዋል።
ለድርድር የማይቀርበው ብሔራዊ ጥቅም እንዲጠበቅ ለማስቻል እንደኾነም አንስተዋል። “የሀገርን ሰላም እና አንድነት ለማስጠበቅ ሁሉም ሊተጋ ይገባል” ብለዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶችን ለማስቀረት እና ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ለማስቻል ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም ጉባዔው በመግለጫው አሳስቧል።
በአራዳ ፓርክ በሚካሄደው ሀገር አቀፍ የምልጃ እና የጸሎት መርሐ ግብር የተለያዩ ተቋማት ተወካዮች እና ግለሰቦች ይሳተፉበታልም ተብሏል።
ዘጋቢ፦ ቤተልሔም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous article“ለሕዝብ ሲባል ከመንግሥት የቀረበልንን የሰላም መንገድ ምርጫችን አድርገናል” የቀድሞ ታጣቂዎች
Next article“ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር በኢኮኖሚ እና ቀጣናዊ ደኅንነት ዙሪያ ስምምነት አድርጋለች” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር