
ደሴ: ግንቦት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ የትጥቅ ትግልን በመተው የመንግሥትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች በኮምቦልቻ የሥልጠና ማዕከል አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ አማካሪ ኮሎኔል ባምላኩ ዓባይ በተለያዩ አካባቢዎች በጫካ የነበሩ ታጣቂዎች የሰላም መንገድን እየመረጡ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በሦሥት ዙሮች ሰላምን ለመረጡ ታጣቂዎች የተሃድሶ ሥልጠና በመስጠት እና በማቋቋም ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጉን አንስተዋል። በዛሬው ዕለትም በኮምቦልቻ እና በጠዳ የሥልጠና ማዕከላት በተመሳሳይ የሰላም መንገድን ለመረጡ ወገኖች የትጥቅ ርክክብ እና አቀባበል እየተደረገ ስለመኾኑ ተናግረዋል።
የትጥቅ ትግልን የመረጡ ታጣቂዎች ለሕዝባችን ያተረፉት ሞት እና እንግልት ብቻ መኾኑን በመገንዘብ አሁንም ቢኾን የክልሉ መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ፈጥነው እንዲቀበሉ ኮሎኔል ባምላኩ ጥሪ አቅርበዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎቹ በቀጣይ ወደ ማኅበረሰቡ ሲቀላቀሉ የሰላም አምባሳደር ኾነው እንዲሠሩ የሚደረግ መኾኑን ያነሱት ኮሎኔሉ በጫካ የሚገኙ ሌሎች ኃይሎችም የሰላምን አማራጭ እንዲቀበሉ አሳስበዋል።
በአቀባበሉ ላይ የተገኙት በብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የሥልጠና ዳይሬክተሩ ብርሃኑ ተስፋዬ ኮሚሺኑ የሰላም መንገድን የመረጡ የቀድሞ ታጣቂዎችን ሥልጠና በመስጠት እና በማቋቋም ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ እየሠራ መኾኑን አንስተዋል።
ኮሚሽኑ በአማራ ክልል የአሁኑን ሳይጨምር በሦሥት ዙሮች የቀድሞ ታጣቂዎችን ወደ ኅብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል።
ከአሚኮ ጋር ቆይታ የነበራቸው የቀድሞ ታጣቂዎችም የተከተሉት መንገድ የተሳሳተ እንደነበር ገልጸዋል።
“በትጥቅ ትግሉ ምክንያት እየተጎሳቆለ ያለው የክልሉ ሕዝብ በመኾኑ ከመንግሥት የቀረበልንን የሰላም መንገድ ምርጫችን አድርገናል” ብለዋል።
በተሳሳተ መንገድ እስከ ዛሬ የበደልነውን ሕዝብ ለመካስ ተዘጋጅተናልም ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ተመስገን አሰፋ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
