
ባሕር ዳር: ግንቦት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምርጫ ዜጎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሀገሬን ይመራልኛል ብለው የሚያምኑትን ፓርቲ ሥልጣን ላይ እንዲወጣ የሚያደርጉበት ሕጋዊ መንገድ ነው።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት መከናወናቸውን የሰሜን ጎጃም ዞን አስታውቋል። የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ አሰፋ ጥላሁን ማኅበረሰቡ ግንዛቤ አግኝቶ የምርጫ ካርዱን በወቅቱ ወስዷል ብለዋል።
በዞኑ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕጋዊ መብታቸውን ተጠቅመው ሀሳባቸውን እንዲያስተዋውቁ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም አንስተዋል።
ምርጫው ነጻ፣ ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ያለ ምንም ተጽዕኖ በገለልተኝነት እንዲጠናቀቅ ሰፊ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን አሥተዳዳሪው ገልጸዋል።
ሕጋዊ እና ተጠያቂነት ያለው መንግሥት ሊመሠረት የሚችለው በምርጫ እና በሕዝብ ይሁንታ ብቻ መኾኑን ማኅበረሰቡ በመገንዘብ ትልቅ ኅላፊነት ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል።
”ማንኛውንም ጥያቄ በዴሞክራሲያዊ መንገድ መፍታት የሥልጣኔ ምልክት ነው፤ ሰላምን ማጽናት እና ሰላም የሰፈነባት ሀገር መገንባት የሚቻለውም በምርጫ ነው ብለዋል።
ሕዝቡ መብቱን በመጠቀም ቀጣይ የሀገሪቱን ዕጣ ፈንታ ሊወስን የሚችል ፓርቲ መምረጥ እንዳለበት ነው የገለጹት። “በድምፅ መምረጥ እና ሰላምን ማጽናት ለነገ የማይተው ኅላፊነቶች ናቸው” ብለዋል አሥተዳዳሪው።
ዴሞክራሲያዊ መንገድ የችግሮች መፍቻ ቀላሉ መንገድ ነው፤
የማኅበረሰቡም ፍላጎት ሊሳካ የሚችለው ሰላም ሲረጋገጥ ብቻ እንደኾነ በመገንዘብ ንቁ የዴሞክራሲ ተሳታፊ መኾን አለበት ሲሉ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
