የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ዳግም ሥራ በመጀመሩ መደሰታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ።

4
ባሕር ዳር: ግንቦት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ)ጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ትልቅ አቅም ያለው ፋብሪካ ነው።
ፋብሪካው በተለያዩ ምክንያቶች ለበርካታ ዓመታት ምርት ሳያመርት መቆዩቱን በተደጋጋሚ አሚኮ መዘገቡ ይታወሳል።
በአሁኑ ወቅት ፋብሪካው ከገጠመው ችግሮች ተላቅቆ ስኳር ማምረት መጀመሩን ከሰሞኑ አሚኮ ከፋብሪካው ሥራ አሥኪያጅ ጋር ቆይታ አድርጎ ዘግቧል።
ፋብሪካው ዳግም ከነበረበት ችግር ወጥቶ ስኳር ማምረት መጀመሩ እንዳስደሰታቸው በፋብሪካው በጥበቃ ከ15 ዓመት በላይ እያገለገሉ ያሉት አቶ ሙላት ያየህ ተናግረዋል።
ፋብሪካው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት ምርት ወደ ማምረት ገብቶ የነበረ ቢኾንም በተለያዩ ምክንያቶች ሥራ ሲያቆም ይቆጫቸው እንደነበረ አስታውሰዋል። ችግሩን መንግሥት ለምን መፍታት አቃተው የሚል ቁጭት በውስጣቸው ይመላለስ እንደነበረም ተናግረዋል።
ኹሉም የመንግሥት አካላት ለፋብሪካው በሰጡት ትኩረት ችግሮቹ ተፈትተውለት ፋብሪካው ወደማምረት መግባቱ የውጥናቸው ስኬት፤ የሕልማቸው እውን መኾን ማሳያ እንደኾነም ገልጸዋል።
ፋብሪካው ሥራ መጀመሩ አሁን ካሉት በተጨማሪ ለአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር በፋብሪካው ያላቸውን ተስፋም ገልጸዋል።
ለቀጣይ ፋብሪካው ሥራ እንዳያቆም ኹሉም ማኅበረሰብ በጉልበት፣ በሃሳብ እና በሌሎች ጉዳዮች እገዛ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል። ሰሞኑንም የአካባቢው ነዋሪዎች አገዳ የመሠብሠብ ሥራ መሥራታቸውን በማሳያነት አንስተዋል።
ፋብሪካውን እንደራሳቸው ንብረት እንደሚጠብቁ የተናገሩት አቶ ሙላት ፋብሪካው ከችግሩ ወጥቶ ሥራ እንዲጀምር ላደረጉ አካላት ምሥጋና አቅርበዋል።
ሌላኛው የአካባቢው ነዋሪ ሼህ ሱሌማን ዑመር በ2004 ዓ.ም የመሠረተ ድንጋይ ሲቀመጥ ቶሎ ግንባታው ተጠናቅቆ ወደ ሥራ ይገባል ብለው ተስፋ አድርገው እንደነበር አንስተዋል። ነገር ግን ለረጅም ዓመታት ወደ ሥራ አለመግባቱ አስቆጭቷቸው እንደነበረ ገልጸዋል። የፋብሪካው ሥራ በመጓተቱም በማኅበረሰቡ ቅሬታ ፈጥሮ ነበረ ነው ያሉት።
ካለፈው ሁለት ዓመት በኋላ ግን መንግሥት በሠጠው ትኩረት ሥራ ዳግም መጀመሩ ትልቅ ደስታ እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።
ፋብሪካው ሥራ መጀመሩ ለጃዊ እና አካባቢው ብቻ ሳይኾን ለሀገሪቱ ያለው ፋይዳ ከፍ ያለ መኾኑን ተናግረዋል። የሥራ ዕድል በመፍጠርም አበርክቶው የጎላ ነው ብለዋል። ፋብሪካው የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል የራሳቸውን ድርሻ እንደሚወጡም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ሰለሞን ስንታየሁ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleየምርጫ ሂደቱ ሕዝቡ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያለው ቁርጠኝነት የታየበት ነው።
Next articleምርጫ ለሀገር!