
ባሕር ዳር: ግንቦት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24/2018 ዓ.ም ታካሂዳለች። ምርጫው ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊነቱን ጠብቆ በስኬት እንዲጠናቀቅም ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ ነው።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሪ ምርጫው የዴሞክራሲ ባሕል የሚጎለብትበት እንዲኾን ከማድረግ ባለፈ በሰላማዊ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ በከፍተኛ ትጋት እየተሠራ ነው ብለዋል። በአሁኑ ወቅት የቅድመ ምርጫ ተግባራት በስኬት እየተመሩ እንደኾነም አስረድተዋል።
በቅድመ ምርጫው ምዕራፍ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ የምርጫ ካርድ ወስዷል። የዘንድሮው የመራጮች ምዝገባ ባለፉት ዓመታት ከነበረው ከእጥፍ በላይ ጨምሯል። ይህም ሕዝቡ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያለውን ከፍተኛ ቁርጠኝነት ያሳያል ነው ያሉት።
የምርጫውን ሰላም ለማስከበር አስተማማኝ የጸጥታ መዋቅር ተመድቦ እየሠራም ይገኛል ብለዋል። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ከምርጫው ሂደት ጋር ተያይዞ ያጋጠመ ምንም ዓይነት የጸጥታ ችግር የለም ብለዋል።
ለዚህ ስኬት የማኅበረሰቡ ትብብር እና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር የተመሠረተው የጋራ ምክር ቤት መድረክ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
እንደ አቶ አወቀ እንዳሉት በዞኑ የፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ በንቃት እና በሰላማዊ መንገድ እየተካሄደ ነው። ለተፎካካሪ ፓርቲዎች በቂ ጥበቃ እየተደረገላቸው እና አማራጮቻቸውን ለሕዝብ እያቀረቡ ይገኛሉም ብለዋል።
ገዥው የብልጽግና ፓርቲም ባለፉት ዓመታት ያከናወናቸውን ስኬቶች እና የነገ ዕቅዶቹን ይዞ ማኅበረሰቡን በሰፊው እያነቃነቀ እንደኾነ ነው የገለጹት። ይህ የፓርቲዎች በነጻነት የመንቀሳቀስ ዕድል ሕዝቡ የሚበጀውን እንዲመርጥ እና የዴሞክራሲ ባሕል እንዲጎለብት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
ዘጋቢ፦ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
