ምርጫን ሰላማዊ ማድረግ የቻሉ ተጽዕኖ ፈጣሪ አንደበቶች !

2
🗳️ባሕር ዳር፡ ግንቦት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገራት የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ንግግሮች በምርጫ ላይ ከፍተኛ አወንታዊ እና አሉታው ተጽዕኖ ፈጥረው አልፈዋል።
ቁልፍ ታሪካዊ የምርጫ ንግግራቸው በዓለም ታሪክ ውስጥ የሀገራትን አቅጣጫ የቀየሩ፤ ሕዝብን ያነቃቁ እና ከፍተኛ የፖለቲካ ተጽዕኖ ያሳረፉም ይኖራሉ።
ታዲያ ሀገርን ከጥፋት በመታደግ ወደ ብርሃን ያሻገሩት እነዚያ ንግግሮች ዛሬም ድረስ ምሳሌ ናቸው።
🗳️🕊️ በምርጫ ወቅት የዴሞክራሲ ሂደትን ለመጠበቅ እና ሰላምን ለማስፈን ማን ምን አለ ?
⚖️ “ሁላችንም የአንዲት ሀገር ልጆች ነን” ኔልሰን ማንዴላ እ.አ.አ በ1994 ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ ሥርዓት ውድቀት ተላቅቃ ባካሄደችው የመጀመሪያ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ወቅት የመፍረስ አደጋ አጋጥሟት ነበር።
በዚህ ወቅት የነጻነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ “ሁላችንም የአንዲት ሀገር ልጆች ነን” የሚል ታሪካዊ የዕርቅ ንግግር በማድረግ ደም መፋሰስን አስቀርተዋል። ምርጫው ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅም አድርገዋል።
🤝🗳️ “የማንኛውም ናይጄሪያዊ ሕይወት እኔ ከማገኘው የፖለቲካ ሥልጣን በላይ ዋጋ አለው” ጉድላክ ጆናታን እ.አ.አ በ2015 ናይጀሪያ ባካሄደችው ምርጫ ጉድላክ ጆናታን ሽንፈታቸውን በጸጋ በመቀበል ለሀገራቸው ታሪክ ሰርተዋል።
“የማንኛውም ናይጄሪያዊ ሕይወት እኔ ከማገኘው የፖለቲካ ሥልጣን በላይ ዋጋ አለው” በማለት በምርጫው መሸነፋቸውን ለሕዝብ በማረጋገጥ ሊፈጠር የነበረን የእርስ በእርስ ግጭት አስቀርተዋል።
ለአፍሪካ የዴሞክራሲ ልምምድም ትልቅ መሠረት እንደጣሉ ነው የሚነገረው።
🇺🇸“ኦባማ የእኔም ፕሬዝዳንት ናቸው” ጆን ማኬይን
እ.አ.አ በ2008 አሜሪካ ባካሄደችው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በባራክ ኦባማ የተሸነፉት ጆን ማኬይን “ኦባማ የእኔም ፕሬዝዳንት ናቸው” በማለት ሽንፈታቸውን በጸጋ በመቀበል ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር አድርገዋል።
ለሀገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦም አበርክተዋል። “ተቃውሞን በጩኸት አትግለጹ፤ ምረጡ” የባራክ ኦባማ የሁሌም ንግግር ነው።
ኦባማ በተለያዬ ጊዜ በአሜሪካ ምርጫ ወቅት ተቃውሟቸውን በጩኸት ለሚገልጹ ዜጎች “አትጩኹ፤ ምረጡ” በማለት እውነተኛ እና ፍሬያማ ለውጥ የሚመጣው በምርጫ ሳጥን ድምጽ በመስጠት ብቻ ነው በማለት ለዓለም አስተምረዋል።
እነዚህን ለማሳያነት ጠቀስን እንጅ በዓለም የምርጫ ታሪክ ከሰው አዕምሮ የማይጠፉ ንግግሮችን ያደረጉ ታዋቂ ሰዎች በርካታ ናቸው። ታሪካዊ ንግግሮቻቸው በወቅቱ ካበረከቱት ፋይዳ ባለፈ አሁንም አስፈላጊ እና አስተማሪ ኾነው ቀጥለዋል።
ኢትዮጵያ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ ጥቂት ቀናት ቀርቷታል። ይህ ምርጫ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ከተጠቀሱት ባለታሪኮች ትምህርት መውሰድ እንዳለባቸው ይታመናል።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleፍትሐዊ የሚዲያ አጠቃቀም ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ 🗳️📺
Next articleየምርጫ ሂደቱ ሕዝቡ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያለው ቁርጠኝነት የታየበት ነው።