የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነፃነት መድረክ የዜጎችን ዕውነተኛ ፍላጎት መሠረት ያደረጉ ፖሊሲዎች እንዲወጡ አግዟል።

6
አዲስ አበባ: ግንቦት 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ያዘጋጀው በስታቲስቲካዊ ሉዓላዊነት እና በተቀናጀ የልማት አሥተዳደር ላይ ያተኮረው ታላቅ ብሔራዊ ጉባኤ በስኬት መካሄዱ ተገልጿል።
በጉባኤው ላይ በሀገሪቱ የስታቲስቲክስ ሥርዓት ላይ የተከናወኑ ዐበይት ተግባራትን በማስገንዘብ፣ ኢትዮጵያ የስታቲስቲክስ ሉዓላዊነቷን ከማረጋገጥ አንጻር ያሳየችውን ተጨባጭ ስኬት እና የደረሰችበትን ጉዞ ማቅረብ ተችሏል ተብሏል።
የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ድኤታ በረከት ፍስሃጽዮን እንዳሉት ከተለያዩ ዘርፎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት በዚህ መድረክ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የሀገሪቱን የስታቲስቲክስ ሉዓላዊነት እና የፖሊሲ ነፃነት አስመልክቶ የሰጧቸው የሥራ መመሪያዎች፣ በቀጣይ የሚከናወኑ ተግባራትን ይበልጥ ውጤታማ በኾነ መንገድ ለመምራት ትልቅ አቅም የሚፈጥሩ ናቸው።
ጉባኤው እስካሁን የተሠሩ ሥራዎችን ከማስገንዘብ ባለፈ የቀጣይ አቅጣጫዎች በግልጽ የተለዩበት መኾኑን
ገልጸዋል። የተቀናጀ የልማት አሥተዳደርን በማረጋገጥ የሕዝባችንን ዕውነተኛ ፍላጎት መሠረት ያደረጉ ፖሊሲዎች እንዲወጡ እና ተግባራዊ እንዲኾኑ መድረኩ ትልቅ ሚና አለው ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ.ር) ይህ ሀገራዊ ጉባኤ በቀጣይ የሚሠሩ የስታቲስቲክስ ሥራዎችን በጥራት እና በስፋት ለማከናወን በእጅጉ ያግዛል ብለዋል። ከተቋማዊ ስኬት ባለፈም፣ በስታቲስቲክስ ሥርዓቱ እና በመረጃ ላይ በተመሠረተ የፖሊሲ አወጣጥ ሂደት ላይ የዜጎች ዕምነት እንዲጨምር፣ በቀጣይ ሀገራዊ አቅጣጫዎች ላይ የጋራ ስምምነት እና መግባባት እንዲፈጠር እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በስፋት ያሳተፈው ይህ ብሔራዊ መድረክ በቀጣይ የሚሠሩ ታላላቅ ሀገራዊ ሥራዎች እና ስታቲስቲካዊ መረጃዎች ለኅብረተሰቡ በስፋት እንዲታወቁ እና ተደራሽ እንዲኾኑ ሰፊ ዕድል የፈጠረ መኾኑ ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ኃይለኢየሱስ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous article“ብልጽግና ቃል የገባውን በተግባር የሚፈጽም ፓርቲ ነው” አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)
Next article“የኑሮ ውድነቱን ለመግታት በጊዜያዊ እና ዘላቂ መፍትሔዎች ላይ ማተኮር ይገባል” ኢብራሂም ሙሐመድ (ዶ.ር)