
ደብረታቦር: ግንቦት 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን የፋርጣ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት እና የንግድ እና ገበያ ልማት ጽሕፈት ቤት በጋራ በመቀናጀት ንግድ እና ባዛር አዘጋጅተዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም ሙሐመድ (ዶ.ር) እንደገለጹት መሰል ባዛሮች መዘጋጀታቸው ሸማቹን እና አምራቹን በቀጥታ በማገናኘት የኑሮ ውድነትን በጊዜያዊነት ለመፍታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው።
በዘላቂነት የገበያ ግሽበቱን ለማረጋጋት ደግሞ የገበያ ማዕከላትን የመገንባት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ጠቁመዋል። የኑሮ ውድነቱን ለመግታት በጊዜያዊ እና ዘላቂ መፍትሔዎች ላይ ማተኮር ይገባል ነው ያሉት።
የፋርጣ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ማዕድነው ብርሃን ባዛሩ በወረዳው የሚገኙ አርሶ አደሮች የሚያመርቷቸውን ምርቶች ለሸማች ማኅበረሰብ ለማስተዋወቅ እና ቋሚ የኾነ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ታስቦ የተዘጋጀ መኾኑን አስረድተዋል።
የፈርጣ ወረዳ ንግድ እና ገበያ ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዋሴ ቸኮለ ሞዴል አርሶ አደሮች ያለ ደላላ ጣልቃ ገብነት ምርቶቻቸውን በቀጥታ ለሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ መቻላቸው አምራቹንም ኾነ ሸማቹን ተጠቃሚ የሚያደርግ ተግባር መኾኑን ገልጸዋል።
የኑሮ ውድነቱን በዘላቂነት ለመፍታት የገበያ ማዕከል መገንባት ወሳኝ መኾኑን ተናግረዋል።
በመድረኩ ላይ የተሳተፉት ምርት አቅራቢዎች የተፈጠረላቸው የገበያ ዕድል አላስፈላጊ መንገላታትን በመቀነስ ምርቶቻቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ በቀጥታ ለሸማቹ ለማድረስ እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።
በዚህም ደስተኛ መኾናቸውን ተናግረዋል። ተግባሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
