“የመስኖ ልማትን በማስፋት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተሠራ ነው” አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

11
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ ዲርማ ወንዝ የመስኖ ፕሮጀክት ግንባታን መርቀዋል።
የልማቱ ተጠቃሚ አርሶ አደሮች የመስኖ ቦይ ግንባታው የአፈር መሸርሸርን በማስቀረት በመስኖ ልማት የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንድንኾን አስችሏል ብለዋል። በዚህም ደስተኛ መኾናቸውን ገልጸዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን ፕሮጀክቱ ከዝናብ ጥገኝነት ለመውጣት እንደሚያስችል አንስተዋል። አርሶ አደሮች በዓመት ሦሥት ጊዜ እንዲያመርቱ እየተሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል።
ምርት እና ምርታማነት እንዲያድግ፣ የገበያ መረጋጋት እንዲፈጠር፣ የኢንዱስትሪ ልማት እንዲያድግ ያደርጋል ነው ያሉት። ፕሮጀክቱ የሥራ ባሕልን የቀየረ፣ የምርት ጥራትን የጨመረ መኾኑንም አንስተዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ደረጀ ማንደፍሮ ግብርናን ከኋላ ቀር አሠራር ወደ ዘመናዊ አሠራር ለመቀየር እየተሠራ ነው ብለዋል። ከዝናብ ጥገኝነት የተላቀቀ፤ በመስኖ የሚያለሙ አርሶ አደሮች ለመፍጠር እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
ፕሮጀክቱ በ16 ወር ይጠናቀቃል ተብሎ ዕቅድ የተያዘ ቢኾንም በሰባት ወር ማጠናቀቅ ተችሏል ነው ያሉት። ማኅበረሰቡን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚያደርግ እና ወጣቱ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲኾን የሚያስችል ነውም ብለዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የመስኖ ልማቱ የደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ደዋ ጨፋ ወረዳ አዋሳኝ ቀበሌዎችን ተጠቃሚ ያደረገ ነው ብለዋል።
ዘመናዊ ግብርናን የመተግበር እና የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ተግባር እየተከናወነ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
የመስኖ ፕሮጀክቱ 290 ሄክታር መሬትን የሚያለማ ሲኾን 490 አባወራዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል። ግንባታው በአጭር ጊዜ በጥራት የተሠራ መኾኑንም አንስተዋል። ፕሮጀክቱ ከተያዘለት ጊዜ ቀድሞ መጠናቀቁንም ገልጸዋል።
የመስኖ ካናሉ በ365 ሚሊዮን ብር መገንባቱንም ገልጸዋል። ለሀገር ቀና የሚያስቡ ሠርቶ መጠቀምን መርህ ያደረጉ ኮንትራክተሮች መኖራቸው የሚደነቅ መኾኑን አንስተው ሌሎች ተቋራጮችም ትምህርት እንዲወስዱ አሳስበዋል።
አዋሳኝ ቀበሌዎችን በልማት ያስተሳሰረ መኾኑ ልማት ድንበር ተሻጋሪ መኾኑን ማሳያ ነውም ብለዋል።
የሙዝ እና የአትክልት ልማቱ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መኾኑን አንስተዋል። አርሶ አደሮች ከሙዝ ባሻገር የማሾ ሰብልን እያለሙ ተጠቃሚ እንዲኾኑ አድርጓል ነው ያሉት። የመስኖ ልማትን በማስፋት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እና የግብርና ዕድገትን ለማዘመን መንግሥት እየሠራ ነውም ብለዋል።
የሥራ ኀላፊዎች በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ በ033 ቀበሌ በ37 ሄክታር መሬት በቦዳ ክላስተር እየለማ የሚገኝ የሙዝ ተክልን ጎብኝተዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleየሚሊሻው ኀይል ዘላቂ ሰላምን እያረጋገጠ ነው።
Next articleሰላምን ከማረጋገጥ በተጓዳኝ ልማቶች እየተሳለጡ ነው።