
ባሕር ዳር: ግንቦት 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሰብዓዊ፣ ቁሳዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት አድርሷል።
በሰሜን ጎጃም ዞን የመራዊ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ብርሃኑ አበራ በጦርነቱ ምክንያት በርካታ ሕጻናት ከሁለት ዓመት በላይ ከትምህርት ገበታ ውጭ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እና ሰላምን ለማረጋገጥ ከኅብረተሰቡ ጋር ሰፋፊ የውይይት መድረኮች ሲካሄዱ መቆየታቸውንም አስታውቀዋል።
ማኅበረሰቡም ከደረሰበት ችግር ወጥቶ ወደ ቀደመው የሰላም ሕይወቱ እንዲመለስ የበኩሉን ጥረት እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት።
በአሁኑ ወቅት የመራዊ ከተማ አሥተዳደር በከፍተኛ የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ መኾኗን ተናግረዋል።
ከ136 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች በመከናወን ላይ ይገኛሉ ነው ያሉት። የልማት ሥራዎቹ በከተማዋ ነዋሪዎች ዘንድ ለረጅም ጊዜ ጥያቄ ኾነው የቆዩ የመሠረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።
የጌጠኛ መንገድ ንጣፍ፣ የከተማ ፋርማሲ ግንባታ፣ የኮሪደር ልማት እና የጎርፍ ማፋሰሻ ቦይዎች ተጠቃሾች እንደኾኑም ገልጸዋል።
በግጭቱ ውድመት የደረሰባቸውን መሥሪያ ቤቶች የመጠገን ሥራም እየተከናወነ ነው። ይህም ሠራተኞች በተገቢው ሁኔታ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ የሚያስችል ነው ብለዋል።
በከተማው ትልቅ ፈተና ኾኖ የቆየውን የማኅበረሰቡን የውኃ ችግር ለመፍታትም በትኩረት እየተሠራ እንደኾነ ገልጸዋል። በተለይም ከከተማ አሥተዳደሩ በተመደበ 5 ሚሊዮን ብር የከርሰ ምድር ውኃ በማውጣት የመራዊን አንደኛ ደረጃ ሆስፒታል የውኃ ችግር መፍታት መቻሉን ማሳያ በማድረግ አንስተዋል።
ሕዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች በቀጣይም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
