የሚሊሻው ኀይል ዘላቂ ሰላምን እያረጋገጠ ነው።

10
ሁመራ: ግንቦት 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሚሊሻ 30ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በተለያዩ አካባቢዎች እየተከበረ ነው።
በዓሉ በዞኑ ዋና ከተማ ሰቲት ሁመራ ከተማ አሥተዳደርም የክልሉ እና የዞኑ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት በደማቅ ወታደራዊ ትርዒቶች ተከብሯል።
የአማራ ክልል ሚሊሻ ኮሚሽን የዘመቻ ዋና መምሪያ ኀላፊ ይታገስ አምባቸው የሚሊሻው ኀይል ለሀገር አንድነት እና ሰላም መከበር ያበረከተውን ውለታ መዘከር ይገባል ብለዋል።
የሚሊሻው ኀይል ዘላቂ ሰላምን እና የሕዝቡን አንድነት በማረጋገጥ ለሁለንተናዊ ልማት ከፍተኛ አሰተዋጽኦ እያበረከተ መኾኑን አንስተዋል።
ዞኑ ነጻነቱን እንዲጎናጸፍ ታላቅ ዋጋ ከከፈሉ የጸጥታ አካላት መካከል ሚሊሻ አንዱ መኾኑን ያነሱት ኀላፊው ይሄንን ነጻነት እና ማንነት አጽንቶ ለመቀጠል የሚሊሻው ሚና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመላክተዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው የዞኑ ሕዝብ እና የጸጥታ መዋቅሩ በእጁ የገባውን ነጻነት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ሰላምን ለማረጋገጥ ከሚሊሻው ኀይል ባሻገር ሁሉም፤ በሁለም ቦታ ዝግጁ እና ቆራጥ ሊኾን ይገባል ነው ያሉት።
የዞኑን ሰላም፣ ልማት እና ማንነት ጠብቆ ለመዝለቅ የተገኘውን ነጻነት እና ማንነት መጠበቅ አስፈላጊ መኾኑንም አንስተዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ጠንካራ የጸጥታ አደረጃጀት በመፍጠር ለአካባቢው ሰላም መረጋገጥ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን አመላክተዋል።
ከፌዴራል የጸጥታ መዋቅር ጋር በመቀናጀት የአካባቢውን ሰላም መጠበቅ መቻሉን ጠቁመዋል። ይሄ ተግባር ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
ሰላምን ማረጋገጥ የሚቻለው በወትሮ ዝግጁነት ነው ያሉት ኮሎኔል ደመቀ ሚሊሻው የሚሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ ለመፈጸም ቁርጠኛ መኾን እንዳለበት ጠቁመዋል።
የበዓሉ ተሳታፊ ሚሊሻዎችም የሚሊሻ ምሥረታ በዓል በመከበሩ ደስታቸውን ገልጸዋል። ከዚህ በፊት የተሰጧቸውን ግዳጆች በቁርጠኝነት መፈጸማቸውን ተናግረዋል። ለሚሊሻው እየተሰጠ ያለው ትኩረት እና ክብር የበለጠ ተነሳሽነትን እንደፈጠረላቸውም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦አምሳሉ አሞኘ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleየከተሞች ገጽታ እና ውበት በፍጥነት እየተቀየረ ነው።
Next article“የመስኖ ልማትን በማስፋት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተሠራ ነው” አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)