
ደብረብርሃን: ግንቦት 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በደብረ ብርሃን ከተማ የተሠሩ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር) የከተሞች ገጽታ እና ውበት ካለፈው ጊዜ በበለጠ በፍጥነት እየተቀየረ መምጣቱን ገልጸዋል። ከተሞች ያላቸውን የተፈጥሮ ጸጋ በአግባቡ በመጠቀም ለመኖር ምቹ እና ውብ እየኾኑ መጥተዋል ብለዋል።
የተጀመሩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን በፍጥነት አጠናቅቆ ለሕዝብ አገልግሎት የማብቃት ባሕል ማደጉንም ገልጸዋል። የኮሪደር ልማት እና የመሶብ አንድ ማዕከል ግንባታዎች አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፋዊ ፈተናዎችን በመቋቋም እየተሠሩ መኾናቸውን አንስተዋል።
ታላላቅ ሥራዎች የተከናወኑት ተግዳሮቶችን ወደ ዕድል በመለወጥ እና አዳዲስ መፍትሔዎችን በመጠቀም ነው ብለዋል።
የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት በከተማው የሦሥት ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ግንባታ በፍጥነት እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የአምስት ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገድ ሥራ በጥራት እየተገነባ መኾኑንም አመላክተዋል።
የመሶብ አንድ ማዕከል ግንባታም የከተማዋን ሁለንተናዊ ዕድገት በሚያፋጥን መልኩ በመከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል። የመጭው ክረምት ዝናብ ከመግባቱ አስቀድሞ የተጀመሩትን ሥራዎች ለማጠናቀቅ አቅጣጫ መቀመጡንም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ለዓለም ለይኩን
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
