የከሚሴ ጠቅላላ ሆስፒታል የእናቶች እና የሕጻናት ሕክምና ማስፋፊያ ፕሮጀክት ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ኾነ።

5

 

ከሚሴ: ግንቦት 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በማስጀመሪያ በመርሐ ግብሩ የተሳተፉ የከተማዋ ነዋሪዎች በማስፋፊያ ፕሮጀክቱ መደሰታቸውን ገልጸዋል። ተገቢውን ጥበቃ ለማድረግ እንደሚሠሩም ተናግረዋል።

የከሚሴ ጠቅላላ ሆስፒታል ሥራ አሥኪያጅ ካሊድ ሙስጠፋ ሆስፒታሉ ከብሔረሰብ አሥተዳደሩ አልፎ ለአጎራባች ዞኖች አገልግሎት የሚሰጥ መኾኑን ገልጸዋል። ማስፋፊያው የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ይረዳል ብለዋል።

ሆስፒታሉ አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል በሠራው ሥራ ወደ ዲጂታል ሥርዓት በመግባት ከወረቀት ንክኪ ነፃ የኾነ አገልግሎት አስጀምሯል ነው ያሉት።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ከ2 ሺህ 500 በላይ እናቶች በሆስፒታሉ እንዲወልዱ መደረጉንም ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት በ114 አልጋዎች ብቻ ሆስፒታሉ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን አንስተዋል። አኹን ላይ ማስፋፊያው በመጠናቀቁ ተጨማሪ 114 አልጋዎችን ወደ ሥራ ማስገባት እንደተቻለ አስረድተዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አህመድ አሊ የሆስፒታሉ ማስፋፊያ በክልሉ ጤና ቢሮ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ የተገነባ መኾኑን ተናግረዋል። የሆስፒታሉን አገልግሎት አሰጣጥ ወደ ሌላ ምዕራፍ የሚያሸጋግር መኾኑን ተናግረዋል።

የሆስፒታሉ ማስፋፊያ በተለይ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ እና የጨቅላ ሕጻናት ሕክምናን ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና ያለው ነው ብለዋል።

ብሔረሰብ አሥተዳደሩ በየደረጃው ያሉ የኅብረተሰብ ጥያቄዎችን ለመፍታት በቅንጅት እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ የክልሉ ጤና ቢሮ የእናቶች እና ሕፃናትን የሕክምና አገልግሎት ለማሻሻል በትኩረት እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።

የሕክምና አገልግሎቱን ቀልጣፋ፣ ዘመናዊ እና ፍትሐዊ ለማድረግ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የማሻሻያ ሥራ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።

ለዲጂታል ሥርዓት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በኹሉም አካባቢዎች ከወረቀት ንክኪ የፀዳ አገልግሎት ለመስጠት እየተሠራ ያለው ሥራም ከፍተኛ ለውጥ እያስመዘገበ መኾኑን ገልጸዋል።

ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም

#አሚኮ_ዜና #ጤና_ማሻሻል #ከሚሴ #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous article“ብልጽግና ፓርቲ ለሴቶች ተጠቃሚነት የሚሠራ ሀገራዊ ፓርቲ ነው” አቶ እንድሪስ አብዱ
Next articleቻይና እና ሩስያ ለዓለም ሰላም በጋራ እንደሚሠሩ አስታወቁ።