ለመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ሪፎርም መሳካት የመሪዎችን ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው።

5
​ባሕር ዳር: ግንቦት 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ሪፎርም በተመረጡ ስምንት ተቋማት የዝግጅት ምዕራፍ ተግባራዊ እየተደረገ መኾኑን የሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ አስታውቋል።
​የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኅላፊ ባንቺአምላክ ገብረ ማርያም ለሪፎርሙ ማስፈጸሚያ የሚኾን ፍኖተ ካርታ፣ አዋጆች፣ ስትራቴጂዎች እና ማኑዋሎች ተዘጋጅተዋል ብለዋል።
በመጀመሪያው ዙር ገንዘብ ቢሮ፣ ገቢዎች፣ ሥራ እና ክህሎት፣ ትምህርት፣ ጤና፤ ግብርና፣ ፕላን እና ልማት ቢሮ እና የሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮን ጨምሮ ስምንት ተቋማት ወደ ዝግጅት ምዕራፍ የገቡ ናቸው ነው ያሉት።
ተቋማቱ የራሳቸውን ዕቅድ እና ኮሚቴ አደራጅተው ተግባራትን እያከናወኑ መኾናቸውን ገልጸዋል።
​በሪፎርሙ የዝግጅት ምዕራፍ አተገባበር ላይ የገጠመውን የግንዛቤ ችግር ለመቅረፍ ከፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር በሦሥት ዘርፎች የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ተሰጥቷል ብለዋል።
የተሰጣቸውን ሥልጠና ወደ ተግባር በመለወጥ በአንድ ማዕከል ተሰባስበው የየተቋማቸውን ሰነዶች እና የአገልግሎት መረጃዎች ያዘጋጃሉ ነው ያሉት።
በሁለተኛው ዙር ከሐምሌ 2018 ዓ.ም በኋላ ወደ አስር ተቋማት ወደ ሪፎርሙ እንደሚገቡም ጠቁመዋል።
ለሪፎርሙ ስኬት የመሪዎችን ቁርጠኝነት፣ የሠራተኞችን ዕውቀት፣ ጊዜ መስጠት እና ለተግባሩ ባለቤት መኾንን የሚጠይቅ ነውም ብለዋል።
ሠራተኞች ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ተቋቁመው ሂደቱን በመልካም ሥነ ምግባር እና በትብብር ሊደግፉት እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous article“ይወክለኛል የምንለውን ፓርቲ መወሰን ያለብን በካርዳችን ብቻ ነው” የዳውንት ወረዳ ነዋሪዎች
Next articleየሚሊሻ 30ኛ የምሥረታ በዓል በሁመራ ከተማ እየተከበረ ነው።