
ባሕር ዳር: ግንቦት 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚካሄድበት ዕለት እየተቃረበ መምጣቱን ተከትሎ በሰሜን ወሎ ዞን ሰፊ የምርጫ ቅስቀሳ እና የዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የመምረጥ መብታቸውን ለመጠቀም በከፍተኛ ተነሳሽነት እና ዝግጁነት ላይ መኾናቸውን ከአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ጋር ቆይታ ያደረጉ የዳውንት ወረዳ ነወሪዎች ነግረውናል።
የዘንድሮው ምርጫ በነጻነት የሚንቀሳቀሱ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች የተለያዩ የፖሊሲ አማራጮች እና ክርክሮች የሚያቀርቡበት በመኾኑ ግንቦት 24ን በጉጉት እንዲጠብቁ እንዳደረጋቸውም ገልጸውልናል። ሀገርን ያሻግራል እና ይወክለናል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ በዝግጅት ላይ መኾናቸውንም አረጋግጠዋል።
ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የሚመራቸውን ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫ ካርድ ማውጣትም ኾነ ድምፅ መስጠት ትልቅ ደስታ እና ዋጋ ያለው የዜግነት ተግባር መኾኑን በኩራት ተናግረዋል።
ምርጫው ፍትሐዊ፣ ተአማኒ፣ አሳታፊ ኾኖ በስኬት እንዲጠናቀቅ እያንዳንዱ ዜጋ የሰላም ባለቤት መኾን እንዳለበትም ነዋሪዎቹ አስገንዝበዋል። “ይወክለኛል የምንለውን ፓርቲ መወሰን ያለብን በካርዳችን ብቻ ነው” ብለዋል ነዋሪዎቹ።
ዘጋቢ፦ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
