
በሰሜን ጎንደር ዞንም ከመራጮች ምዝገባ ጀምሮ የቅድመ ዝግጅት ሥራው ቀጥሏል።
የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ የዞኑ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ የመራጭነት ካርድ መውሰዱን ተናግረዋል።
ኹሉም ፓርቲዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ እንዲያደርጉ በተሰጠው አቅጣጫ መሠረትም በዞኑ የምረጡኝ ቅስቀሳ በተደራጀ አግባብ በፓርቲዎች እየተደረገ መኾኑን ተናግረዋል። ሕዝቡም በነቂስ ወጥቶ በምርጫ ቅስቀሳ መድረኩ ላይ እየተሳተፈ ነው ብለዋል።
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ እንደ ዞን የተሻለ ዝግጀት መደረጉን ገልጸዋል። ሕዝቡም በምርጫው ሂደት የተሻለ ተሳትፎ እያሳየ መኾኑን ነው ያነሱት።
በዞኑ በኹሉም የምርጫ ክልሎች እና ጣቢያዎች የተደራጀ የጸጥታ ኀይል ሥምሪት ያለ በመኾኑ የቅድመ ምርጫ ሂደት ሰላማዊ ነው ብለዋል።
ሰላሙን አጽንቶ ለማስቀጠል አና ምርጫውን በሰላማዊ መንገድ ለማጠናቀቅ በቂ ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት ።
የዞን አሥተዳደሩ የመንግሥት መዋቅር ከመራጮች ምዝገባ ሂደት ጀምሮ በየምርጫ ክልሎች እና ጣቢያዎች ለሚገኙ አስፈጻሚዎች የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በወቅቱ የማሟላት ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝም ነው ዋና አሥተዳዳሪው ያረጋገጡት።
ሕዝቡ ያደሩ የልማት ጥያቄዎች ቢኖሩትም ጥያቄዎቹ የሚፈቱት የተጠናከረ መንግሥት ሲኖር ነው የሚል ጽኑ አቋም አለው ብለዋል። ጠንካራ መንግሥት የሚመሠረተው ደግሞ በሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ መኾኑን ተገንዝቧል ነው ያሉት።
ጠንካራ መንግሥት መምረጥ እና መመሥረት ደግሞ በምርጫ ሂደት የሚወሰን በመኾኑ በሂደቱ ሕዝቡ ይወክለኛል የሚለውን የመምረጥ መብት እና ኀላፊነቱን ለመጠቀም እየተንቀሳቀሰ መኾኑን አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
