ምርጫው ወጣቶች የሰላም አምባሳደርነታቸውን የሚያረጋግጡበት ነው።

8
🗳️ 🕊️ባሕር ዳር፡ግንቦት 12/2018 (አሚኮ) ኢትዮጵያ የቀጣይ አምስት ዓመታት መሪዋን ልትመርጥ ቀናቶች ቀርተዋታል። እስካሁን ባለው የምርጫ ሂደት የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች ሲደረጉ ቆይተዋል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ዮሴፍ አበራ በሀገር አቀፍ ደረጃ 55 ሲቪክ ማኅበራት የሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ እንዲታዘቡ እና እንዲያሥተባብሩ በምርጫ ቦርድ እውቅና እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።
ከእነዚህ ውስጥም 32 ሺህ 500 የሚኾኑ ወጣቶች የምርጫውን ፍትሐዊነት እንዲታዘቡ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሥምሪት ተሰጥቷቸዋል ነው ያሉት።
እነዚህ ታዛቢ ወጣቶች ከምርጫ ቦርድ ባጅ መረከባቸውንም ገልጸዋል። ምርጫውን እንዴት መታዘብ እንዳለባቸውም የመራጮች ትምህርትን ጨምሮ ሰፊ ግንዛቤ እየተፈጠረላቸው መኾኑን ተናግረዋል።
ታዛቢዎች ምርጫ ቦርድ በሚያስተላልፋቸው መረጃዎች እና የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን በሚሰጣቸው አቅጣጫ ብቻ በመታገዝ ምርጫውን ገለልተኛ ኾነው እንዲታዘቡም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ምርጫውን ነጻ እና ገለልተኛ ኾኖ በመታዘብ ፍትሐዊነቱን ለማረጋገጥ ዝግጁ መኾኑንም አቶ ዮሴፍ አረጋግጠዋል።
“ኢትዮጵያን ለማሻገር ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የዚህ ዘመን አደዋ ነው” ብለው እንደሚያስቡ የሚናገሩት ዋና ሥራ አሥፈጻሚው ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ከሲቪክ ማኅበራት አደረጃጀቶች በተጨማሪ የሀገሪቱ ወጣቶች ሚናም ከፍተኛ መኾኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
በምርጫው ወጣቶች በመራጭነት፣ በተመራጭነት፣ በታዛቢነት፣ በማሥተባበር እና በሌሎች የምርጫ ሂደቶች ሰፊ ተሳትፎ እያደረጉ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። ይህም ወጣቶች በምርጫው ከተመልካችነት የወጡበት እና ባለቤት መኾናቸውን ያረጋገጡበት ነው ብለዋል።
“ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ወጣቱ የሰላም አምባሳደርነቱን የሚያረጋግጥበት መኾን አለበትም” ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ !
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous article⚖️ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁሉን አቀፍ የፍትሕ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ሊገነባ ነው።
Next articleልማትን በመንግሥት ፣ መንግሥትን በምርጫ