
ባሕር ዳር: ግንቦት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁሉን አቀፍ የኾነ የፍትሕ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ወይም “ጀስቲስ ሀብ” ለመገንባት ዲዛይን አሠርቷል።
የተዘጋጀው የመነሻ ዲዛይንም የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በተገኙበት ተገምግሟል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው የሚገነባው ማዕከል የክልሉን የፍትሕ ሥርዓት ለማዘመን እና ነጻ የዳኝነት አገልግሎትን ለመገንባት እንዲሁም አማራጭ አለመግባባት መፍቻ ሥርዓቶችን በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ ለታቀደው የ25 ዓመት የአሻጋሪ የልማት ዕቅድ አካል ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ለክልሉ ብቻ ሳይኾን ሀገራዊ፣ አሕጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ፋይዳ ያለው በርካታ አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል ለማቅረብ የሚያስችል መኾኑንም ገልጸዋል።
የሚገነባው ማዕከል በውስጡም አራት የሚኾኑ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ይኖሩታል ብለዋል።
👉 በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዙሪያ የሚነሱ አለመግባባቶችን ከመደበኛ ፍርድ ቤት ውጪ ለመፍታት የሚያስችለው “የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ የዕርቅ እና የግልግል ዳኝነት ማዕከልን” ይዟል።
👉 በሕግ የበላይነት እና በሰላም ጉዳዮች መከላከል ዙሪያ ጥናት እና ምርምር የሚያደርግ “የጣና የሕግ የበላይነት እና የሰላም የልህቀት ማዕከል” የሚል ተቋም ይኖረዋል።🕊️
👉”የዓባይ ብሔራዊ የፍትሕ ሙዚዬም” የተባለ ከዚህ ቀደም የነበሩትን የፍትሕ ሥርዓት ታሪኮች ለትውልድ ለማስተላለፍ ለጥናትና ምርምር እንዲውሉ ለማድረግ ታስቦ የሚዘጋጅ ማዕከልም ይኖረዋል።
👉 ዘመናዊ ፋሲሊቲዎች የተሟሉለት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በማዕከሉ ውስጥ የሚገነባ ይኾናል ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ።
ፕሮጀክቱ ከፍትሕ አገልግሎት ባለፈ ባሕር ዳር ከተማን የፍትሕ ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እንዲያግዝ ተደርጎ ከከተማዋ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ፣ ከጣና ሐይቅ እና ከዓባይ ወንዝ መነሻ ጋር ተሳስሮ የሚገነባ ስለመኾኑም አብራርተዋል።
በውይይቱ ማጠቃለያ ላይም ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ፕሮጀክቱን አሥመልክቶ በቀጣይ ሊሠሩ ስለሚገባቸው ጉዳዮች አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
#አሚኮ #ጠቅላይ_ፍርድ_ቤት #ኢትዮጵያ 🇪🇹
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ !
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
