በደቡብ ጎንደር ዞን እና በደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር የተገነቡ መሠረተ ልማቶች ለአገልግሎት ክፍት ኾኑ።

5
ደብረታቦር፡ ግንቦት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል፣ በደቡብ ጎንደር ዞን እና በደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በከተማዋ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት የበቁ እና በመገንባት ላይ ያሉ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን ጎብኝተዋል።
ከተጎበኙት መካከል የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ያስገነባው ባለ 2 ወለል የላብራቶሪ ማዕከል አንዱ ነው።
ማዕከሉ ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የሕክምና መሣሪያዎች ተሟልተውለት ሥራ መጀመሩን የከተማዋ ጤና መምሪያ ኀላፊ በረከት ደስታ ገልጸዋል።
ማዕከሉ በደብረታቦር እና በደቡብ ጎንደር ዞን ለሚገኙ 10 ሆስፒታሎች ሙሉ የላብራቶሪ አገልግሎት በመስጠት የማኅበረሰቡን ችግር እንደሚፈታም አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል በክልሉ ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ እና በከተማ አሥተዳደሩ በጋራ በ100 ሚሊዮን ብር ወጭ የተገነባው የሰኞ ገበያ 2ኛ ደረጃ የገበያ ማዕከል ተመርቋል።
የደብረታቦር ከተማ ከንቲባ ደሴ መኮነን እና የከተማዋ ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ታድሎ ድረስ እንደገለጹት ማዕከሉ አምራቾችን፣ ነጋዴዎችን እና ሸማቾችን በቀጥታ በማገናኘት እና የ15 በመቶ ቅናሽ በማድረግ አሁን ያለውን የኑሮ ውድነት እና የገበያ አለመረጋጋት ለመፍታት ታስቦ የተገነባ ነው።
የክልሉ ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም ሙሐመድ (ዶ.ር) ግንባታው የተራዘመውን የግብይት ሰንሰለት እንደሚያሳጥር ገልጸው የጅምላ ነጋዴዎች እና ሸማቾች በቅንጅት እንዲሠሩ አሳስበዋል።
በተጨማሪም ግንባታው ከ85 በመቶ በላይ የደረሰው የሞሰብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሕንፃ የተጎበኘ ሲኾን ፕሮጀክቱ በአጭር ጊዜ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ የከተማዋ ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት መምሪያ ኀላፊ ዓባይ አለባቸው ለጎብኝዎቹ አስረድተዋል።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ !
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleበጽንፈኛ ቡድኑ ላይ ጠንካራ እና የተቀናጀ እርምጃ መወሰዱን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ክፍለ ጦሮች አስታወቁ።
Next articleበሰሜን ሜጫ ወረዳ ሲገነቡ የቆዩ የተለያዩ መሠረተ ልማቶች ተመረቁ።