ለ15 ሺህ ዜጎች አገልግሎት መስጠት የሚችል ጤና ጣቢያ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ኾነ።

9
ጎንደር :ግንቦት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ታች አርማጭሆ ወረዳ አሸሬ ከተማ 126 ሚሊዮን ብር ወጭ የተደረገበት ጤና ጣቢያ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ኾኗል።
የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት ከ30 እስከ 60 ኪሎ ሜትር ይጓዙ እንደነበር የነገሩን የአሸሬ ከተማ ነዋሪዎች በጤና ጣቢያው መከፈት ደስታቸውን ገልጸዋል።
‎ጤና ጣቢያው ተገቢውን ግልጋሎት እንዲሰጥ የበኩላቸውን ኀላፊነት እንደሚወጡም አንስተዋል።
‎በክልሉ በጀት የተገነባው ጤና ጣቢያው አንድ ዓመት የግንባታ ጊዜ እንደጨረሰ የታች አርማጭሆ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ አስማረ የኋላሸት ተናግረዋል።
‎ጤና ጣቢያው ከ10 እስከ 15ሺህ ዜጎች አገልግሎት እንደሚሰጥም አንስተዋል።
‎የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሬ ጤና ጣቢው በአካባቢው መገንባቱ የበርካታ ዜጎችን እንግልት ይቀንሳልም ብለዋል።
‎የጤና ጣቢያውን አስፈላጊ ግብዓት ለማሟላት እንደሚሠሩም ዋና አሥተዳዳሪው ጠቅሰዋል። በተለይ የመድኃኒት፣ የሰው ኀይል እና መሰል ግብዓቶችን ለማሟላት በትኩረት እንደሚሠራም አመላክተዋል።
‎ጤና ጣቢያው ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጥ የአካባቢው ነዋሪዎች የህክምና ተቋሙን እንዲንከባከቡም ጠይቀዋል።
‎ጤና ጣቢዎችን ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መኾኑን ያነሱት ደግሞ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ኀላፊ ሲስተር ምሳ ታረቀኝ ናቸው።
‎ታች አርማጭሆ ወረዳ ወባ በስፋት የሚከሰትበት አካባቢ በመኾኑ የጤና ጣቢያው መከፈት ችግሩን እንደሚያቃል አንስተዋል።
‎የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ምክትል ኀላፊ አደራጀው ካሤ ለጤና ጣቢያው የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች እንዲሟሉ ቢሯቸው እንደሚሠራ ተናግረዋል።
‎የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ በወረዳው እየተሠሩ ያሉት የእናቶች የወሊድ ማቆያ ተግባራት የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል።
‎መንግሥት ጽዱ እና ለታካሚዎች ምቹ የህክምና ከባቢ ለመፍጠር አልሞ እየሠራ ነው ያሉት ኀላፊዋ በቀጣይም አገልግሎቱን ለሌሎች ተደራሽ ለማድረግ ሥራውን ማዘመን ይገባልም ብለዋል።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ !
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous article“ብልጽግና ቃል የገባውን በተግባር ፈጽሞ አሳይቷል” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)
Next articleየስፖርት ዘርፉን የቱሪዝም አቅም አድርጎ መጠቀም ያስፈልጋል።