5
🗳️ 🇪🇹ባሕር ዳር፡ ግንቦት 11/2018 (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች ማኅበራት ፌዴሬሽን “የሲቪክ ማኅበራት ሚና ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ” በሚል መሪ መልዕክት ለምርጫ ታዛቢ የሴቶች እና ወጣቶች የሲቪክ ማኅበራት አደረጃጀቶች ሥልጠና ሰጥቷል።
የባሕር ዳር ከተማ ሴቶች ማኅበራት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ዘውድዓለም ወረታው በከተማ አሥተዳደሩ ለምርጫ ታዛቢነት ተመርጠው ለምርጫ ቦርድ ከተላኩት 133 ታዛቢዎች መካከል 125 ለሚኾኑት ባጅ ተዘጋጅቶ እንደተላከላቸው ገልጸዋል።
እየተሰጠ የሚገኘው ሥልጠናም ታዛቢዎቹ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሐዊነትን በአግባቡ እንዲታዘቡ ለማስቻል ነው ብለዋል።
የአማራ ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ግርማ አሸነፍ እንደ ሀገር 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለመታዘብ እና ለማስተባበር በፌዴራል ምርጫ ቦርድ ዕውቅና ከተሰጣቸው 55 ማኅበራት መካከል የአማራ ወጣቶች ማኅበር፣ የአማራ ሴቶች ማኅበራት ፌዴሬሽን እና የአማራ ወጣቶች ፌዴሬሽን እንደሚገኙበት ተናግረዋል።
እነዚህ አደረጃጀቶች ምርጫው ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ታሪካዊ አሻራቸውን እንዲያሳርፉም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሙሕዲን ናስር የሴቶች እና የወጣቶች ፌዴሬሽን ምርጫን በመታዘብ እና በማስተባበር ከፍተኛ ኀላፊነት እንዳለባቸው ጠቅሰዋል።
ታዛቢዎች አድልኦ በሌለበት እና በፍትሐዊ መንገድ ምርጫውን ለመታዘብ ቃል መግባታቸውን በመጥቀስ ምርጫውን ከወገንተኝነት፣ ከአድልኦ እና ከተጽዕኖ ነጻ ኾኖ በመታዘብ የሴቶችን እና የወጣቶችን ሲቪክ ማኅበራት ተዓማኒነት ማረጋገጥ ያስፈልጋልም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ዮሴፍ አበራ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫን ፍትሐዊነት የሚታዘቡ 32 ሺህ 500 ወጣቶች በሀገር አቀፍ ደረጃ መሠማራታቸውን አሳውቀዋል።
ታዛቢዎቹ ገለልተኛ ኾነው ምርጫው ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲኾን የድርሻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ባካሄደቻቸው ምርጫዎች ከውጭ የመጡ አካላት ምርጫውን ይታዘቡ እንደነበር አስታውሰዋል። በዘንድሮው ምርጫ ግን ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ተመልካች ከመኾን ወጥተው የምርጫውን ፍትሐዊነት ራሳቸው በመታዘብ ፍትሐዊነቱን ማረጋገጥ እንዲችሉ ተሠርቷል ነው ያሉት።
በሥልጠናው የተሳተፉ የምርጫ ታዛቢዎች በበኩላቸው በሥልጠናው ባገኙት ግንዛቤ መሠረት የመራጭነት ካርድ የወሰደ ማንኛውም ዜጋ ይወክለኛል የሚለውን አካል በነጻነት እንዲመርጥ እና ምርጫው ፍትሐዊ እንዲኾን ኀላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁ እንደኾኑም አረጋግጠዋል።
በመድረኩ የባጅ ርክክብ ሥነ ሥርዓትም ተካሂዷል።
ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ !
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous article“በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለማቋቋም ቃል የገባነውን በተግባር አረጋግጠናል ” አብዱ ሁሴን (ዶ.ር )
Next article“ብልጽግና ቃል የገባውን በተግባር ፈጽሞ አሳይቷል” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)