“በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለማቋቋም ቃል የገባነውን በተግባር አረጋግጠናል ” አብዱ ሁሴን (ዶ.ር )

4

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦ ወረዳ የተገነቡ መሠረተ ልማቶችን መርቀዋል።

የወረባቦ ወረዳ የውኃ እና ኢነርጅ ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እና የወረዳው ምክትል አሥተዳዳሪ መሀመድ ሰኢድ ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ኬላዎች፣ የንጹሕ መጠጥ የውኃ መሠረተ ልማቶች እና የእናቶች ማዋለጃ ክፍል መገንባቱን ገልጸዋል።

በወረዳው 52 ፕሮጀክቶች መሠራታቸውን ተናግረዋል።
ፕሮጄክቶቹ ከ543 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ተደርጎባቸዋል ብለዋል። በ2018 በጀት ዓመት የሕዝብን ጥቅም የሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውንም ገልጸዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን በዞኑ 110 ፕሮጀክቶች እየተመረቁ ነው ብለዋል። ልማቶቹ ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ ተደርጎባቸዋል ነው ያሉት።

ጤና ጣቢያዎች፣ ትምህርት ቤቶች እና የንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ፕሮጀክቶች ሰፊ ሽፋን መያዛቸውን ተናግረዋል። የመሠረተ ልማት ግንባታዎቹ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳላቸውም አንስተዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የተመረቁ መሠረተ ልማቶች ፕሮጀክቶችን የመፈጸም አቅም ማደጉን እና የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እያገኙ መኾኑን ማሳያ ናቸው ብለዋል።

ፕሮጀክቶቹ የመልካም አሥተዳደር እና የልማት ጥያቄዎች በዘላቂነት እንደሚፈቱ ማሳያ መኾናቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ በስፋት የሚነሱ ጥያቄዎች የመንገድ፣ የንጹሕ መጠጥ ውኃ እና የጤና ተቋማት እንደኾኑ እና ጥያቄዎችን ለመመለስም መሠራቱን ተናግረዋል።

በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለማቋቋም ቃል የገባነውን በተግባር አረጋግጠናልም ነው ያሉት።

በክልሉ መንግሥት እና በወረዳው ትብብር መሠራታቸውንም ገልጸዋል። ብልጽግና በችግር ውስጥ ዕድልን በመመልከት ችግርን አልፎ አመርቂ የልማት ሥራዎች ማልማት ችሏል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል ልማት እንዲያብብ በማድረግ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር ለማሳደግ ብልጽግና እየሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል።

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

#አሚኮ_ዜና #መሠረተ_ልማት #ወረባቦ_ደቡብወሎ #ኢትዮጵያ🇪🇹

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article📺 🎙️ ሚዲያው የግብርና እና የእንስሳት ልማት ሥራዎችን ግንባር ቀደም አጀንዳ ሊያደርጋቸው ይገባል።