
ባሕር ዳር: ግንቦት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ከምሥራቅ ጎጃም ዞን እና ከወረዳ መሪዎች ጋር በመኾን የቢቸና መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልን የአገልግሎት አሰጣጥ እና የመድኃኒት አቅርቦት ገምግመዋል።
የጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ መልካሙ ጌትነት በግምገማው የጤና ቢሮ ብቃት ያለው የሰው ኀይል ለመገንባት ከጤና ኤክስቴንሽን ጀምሮ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የሙያ ምድብ ያልነበራቸውን ከ1 ሺህ በላይ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የሙያ ምድብ እንዲያገኙ የተደረገ ሲኾን፤ ወደ ደረጃ አራት ለማድረስ በተሠራው ተከታታይ ሥራ በአሁኑ ወቅት በደረጃ ሦሥት ላይ የሚገኙት ከ400 የማይበልጡት ብቻ መኾናቸውን አብራርተዋል።
በዲፕሎማ ደረጃ ያሉ የጤናው ዘርፍ ሠራተኞችም የሙያ ደረጃቸውን የሚያሻሽሉበት ሥርዓት ተዘርግቶ በዚህ በጀት ዓመት ብቻ 1ሺህ 750 ባለሙያዎችን ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማስገባት መቻሉን ጠቁመዋል።
ሌሎች የሙያ ደረጃዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲያድጉ ይደረጋል ያሉት አቶ መልካሙ፤ የጤና ሥርዓቱን ለማዘመን ዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎችን በማቅረብ፣ የታካሚዎችን መረጃ በዲጂታል ሥርዓት ማደራጀት፣ ጽዱ የጤና ተቋምን መፍጠር፣ እንዲሁም በቂ መድኃኒት እና የቴክኖሎጂ ድጋፍ እንዲኖር ጤና ቢሮው በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በምሥራቅ ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ገነት በቀለ በበኩላቸው፤ የሆስፒታሉን አገልግሎት እና የጤና ቢሮውን ድጋፍ አድንቀዋል። በቀጣይም ማኅበረሰቡን በማስተባበር ከቢቸና ከተማ አሥተዳደር እና ከእነማይ ወረዳ መሪዎች ጋር በመኾን የምሥራቅ ጎጃም ዞን ለሆስፒታሉ የቅርብ ክትትል እና ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
#አሚኮ_ዜና #የጤና_ሥርዓትን #ማዘመን_ቢቸና #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ🇪🇹
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
